በኢትዮጵያ የነበሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቶችን ለማቅናት የተጀመረው የሪፎርም ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገቡን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በ7ኛው የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ተገኝተው ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው።
ከሪፎርሙ በፊት በመደበኛው የባንክ የውጭ ምንዛሪ ተመን እና በጥቁር ገበያው መካከል የነበረው የ110 በመቶ ልዩነት በአሁኑ ወቅት ወደ 13 በመቶ ዝቅ ማለቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ይህም በኢኮኖሚው ላይ ጤናማ ምልክት መታየቱን እንደሚያረጋግጥ አስረድተዋል።
ባለፈው ዓመት ከ33 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማስገባት መቻሉን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህም የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከ20 በመቶ በላይ ዕድገት ማሳየቱን አብራርተዋል።
በተጨማሪም የወጪ ንግድ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲሁም የሐዋላ ገቢ ማደጉን እና በተሠራው የዕዳ ሽግሽግ ሥራ የዕዳ ጫና ወደ መካከለኛ ደረጃ መውረዱን ተናግረዋል።
በሪፎርም ሂደቱ የተፈጠረውን ጫና ለመቋቋም መንግሥት የደመወዝ ጭማሪ፣ ድጎማ እና በወሳኝ ምርቶች ላይ የቀረጥ ነጻ ዕድሎችን ተግባራዊ ማድረጉን አስታውሰዋል።
በቀጣይም የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ሠራተኞችን ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል በሕግ ለመወሰን ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።
የዋጋ ግሽበት በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በኢትዮጵያ አሁንም ፈተና ሆኖ መቀጠሉን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሕዝቡን የኑሮ ጫና ለማቃለል በርብርብ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
በዓይናለም ሃድራ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: