አባቶች በደምና በአጥንታቸው ዳር ድንበሯን አስከብረው ያወረሷትን ታላቅ ሀገር፣ የአሁኑ ትውልድ ከልመናና ከጥገኝነት በተላቀቀ አዲስና ታሪካዊ መንገድ እውነተኛ ሉዓላዊነቷን እያረጋገጠላት እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዛሬ ጳጉሜን 1 የእመርታ ቀንን በማስመልከት ባስተላለፉት መልእክት፤ ኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር በማውጣት ስንዴ ከማስገባት ተላቃ ዛሬ የአፍሪካ ቀዳሚ የስንዴ አምራች መሆን መቻሏንና በዚህም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪን ማስቀረት እንደተቻለ አመልክተዋል።
በግብርናው ዘርፍ በ«ሌማት ትሩፋት» መርሐ ግብር የምግብ ዋስትናን በተግባር የማረጋገጥ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ«ኢትዮጵያ ታምርት» ንቅናቄም አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋትና ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር የሀገርን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት የማጠናከር ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል።
ከዚህ ቀደም «አይነኬና የማይደፈሩ» ተብለው ይታሰቡ የነበሩ ከባድ የማክሮ-ኢኮኖሚ ሪፎርም ውሳኔዎች በቁርጠኝነት ወደ ተግባር መተርጎማቸውን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህ ታሪካዊ እርምጃዎች የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በፅኑ መሠረት ላይ ለመገንባት ማስቻላቸውን ገልጸዋል።
እነዚህ የተመዘገቡ ታላላቅ ድሎች ኢትዮጵያ በሚያጋጥሟት ማናቸውም ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች ሸብረክ ሳትል በፅናት የመጓዝ አቅሟን የሚያረጋግጡ ህያው ምስክሮች መሆናቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እየተከናወነ ያለው ሀገራዊ የእመርታ ጉዞ ለመጪው ዓመት እጅግ ግዙፍ ተስፋን የሰነቀ መሆኑን አረጋግጠዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: