ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ጸጋ የታደለች እና በማዕድን ሀብት የከበረች ምድር ብትሆንም ለበርካታ ዓመታት ይህን እምቅ ሀብቷን በሚገባ ሳትጠቀምበት ቆይታለች። ይሁን እንጂ ይህን እምቅ ሀብት ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በመቀየር ረገድ አሁን ላይ ጠንካራ መሠረት ተጥሏል።
አዲሱ ዓመት የዕድገታችንን ጉዞ ይበልጥ የምናፋጥንበት በተለይም የማዕድን ዘርፉን ወደ አዲስ ከፍታ የምናሸጋግርበት የብሩህ ተስፋ ዘመን መሆኑን የቅርብ ጊዜ አፈጻጸሞች በግልጽ ያሳያሉ።
የማዕድን ዘርፉ ቀደም ሲል ለአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ያበረክት የነበረው ድርሻ አነስተኛ ቢሆንም፣ አሁን ግን በተወሰዱት የፖሊሲ እና የተቋማዊ ሪፎርም እርምጃዎች የኢኮኖሚ ዕድገታችን ወሳኝ ሞተር ሆኖ ብቅ ብሏል።
በ2018 በጀት ዓመት የተመዘገበው አበረታች የውጭ ምንዛሪ ገቢ እና ከውጭ ይገቡ የነበሩ የኢንዱስትሪ ማዕድናትን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉ ዘርፉ ለኢኮኖሚ ዕድገት እያበረከተ ያለውን ወሳኝ እና ታሪካዊ ሚና በተግባር የሚያረጋግጡ ትልልቅ ስኬቶች ናቸው።
በተለይም የድንጋይ ከሰልን ጨምሮ ሌሎች የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ በስፋት በማምረት በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ ማዳን መቻሉ የንግድ ሚዛንን በማስተካከል በኩል የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ይህ የተጀመረው ስኬት የትልቁ ጉዟችን መጀመሪያ እንጂ መድረሻችን አይደለም። በቀጣይም ዘርፉ ለሀገር ውስጥ ምርት የሚያበረክተውን ድርሻ ይበልጥ ለማሳደግ እና ኢኮኖሚውን በጠንካራ መሠረት ላይ ለመገንባት ግልጽ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎች ተይዘው እየተሠራ ነው።
ከእነዚህም መካከል የማዕድን ሀብትን ከጥሬ ዕቃ አቅራቢነት ብቻ አውጥቶ እሴት ወደ ተጨመረበት ምርት የመቀየር ስትራቴጂ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። ይህ አካሄድ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ከማሳደግ ባሻገር ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድልን ይፈጥራል፤ የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪንም በጽኑ መሠረት ላይ ያቆማል።
በተጨማሪም እንደ ወርቅ፣ እብነ በረድ፣ ጌጣጌጥ እና ሌሎች የኢንዱስትሪ ማዕድናት ላይ በማተኮር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ በግል ኢንቨስትመንት እና በተጠናከረ የመንግሥት ተቋማዊ አቅም በመደገፍ ለልማት የላቀ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው።
ይህንኑ ጥረት ለማገዝ ዘመናዊ የማዕድን መሠረተ ልማት እና የተቀናጀ የመረጃ ሥርዓትን በመገንባት ኢትዮጵያ ካላት እምቅ ሀብት ጋር የሚመጣጠን ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንድታገኝ ሰፊ ሥራ በመሠራት ላይ ነው።
የማዕድን ዘርፋችን ነገን አሻግሮ ለሚያይ ትውልድ የተዘረጋ ጠንካራ የኢኮኖሚ ድልድይ ነው። ከተፈጥሮ ጸጋችን ጋር ቴክኖሎጂን እና ጠንካራ የሰው ጉልበትን አዋህደን፣ የኢትዮጵያን ብልጽግና የምናረጋግጥበት ጊዜ አሁን ነው።
አዲሱ 2019 ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የሥራ እና የማዕድን ዘርፉ በተስፋ አብቦ ታላቅ ሀገራዊ ዕድገት የምናስመዘግብበት የብሩህ ተስፋ ዓመት ይሁንልን!
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: