በካቲት 21 ቀን 2018 ዓ.ም አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የሰነዘሩትን የተቀናጀ የአየር እና የሚሳይል ጥቃት ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት ስድስት ወራትን አስቆጥሯል።
በሳምንታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ቢታሰብም በፍጥነት እስከ ካስፒያን ባህር ድረስ በመስፋፋት አጠቃላይ የመካከለኛውን ምስራቅ እና የዓለም አቀፉን የጂኦፖለቲካዊ ስርዓት ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ከቶታል።
አሜሪካ በጦርነቱ መጀመሪያ የኢራንን የኒውክሌር አቅም፣ የባሊስቲክ ሚሳይል ክምችት እና የባህር ኃይል ሙሉ በሙሉ የመደምሰስ እንዲሁም የስርዓት ለውጥ የማምጣት ግብ ይዛለች የሚል ትችት ይሰነዘርባታል።
ይህም ቢሆን ከተደጋገሙ ጥቃቶች በኋላም ቴህራን አሁንም የኒውክለር ጦር መሣሪያ ለመሥራት የሚያስችል 440 ኪሎ ግራም ከፍተኛ ደረጃ የዳበረ ዩራኒየም በእጇ ይዛ እንደምትገኝ ነው የሚገለጸው።
በሌላ በኩል የአሜሪካን ጥቃት በመቋቋም እና ቀጣናዊ ተኪ ቡድኖቿን በማንቀሳቀስ ህልውናዋን ማስጠበቅ የቻለችው ኢራንም ብትሆን፣ ከ82 በመቶ በላይ የሚሆነው የሚሳይል ክምችቷ በመውደሙ እና ወታደራዊ መሰረተ ልማቶቿ በመመተታቸው ከፍተኛ የሰው እና የቁሳቁስ ጉዳት አስተናግዳለች።
ከዓለም አቀፍ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ዝውውር ከአንድ አምስተኛ በላይ የሚያልፍበት የሆርሙዝ የባህር ሰርጥ መዘጋት ደግሞ የዓለም አቀፉን የኢኮኖሚ አቅም አናግቱያል።
የመርከቦች እንቅስቃሴ በመቀነሱ የተከሰተው የነዳጅ ዋጋ ንረት በአሜሪካ የነዳጅ ዋጋ በእጥፍ እንዲጨምር በማድረግ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ የፖለቲካ ተቃውሞ አስከትሏል።
በኢራን በኩል ደግሞ የገንዘብ እሴት መውደቅ፣ የነዳጅ ገቢ ማጣት እና የኑሮ ውድነት የከፋ የኢኮኖሚ ውጥረት ፈጥሯል።
ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን በተመለከተ፣ የአሜሪካ የኔቶ እና የባህረ ሰላጤው አጋሮች ቀጥተኛ ወታደራዊ ተሳትፎ ከማድረግ የተቆጠቡ ቢሆንም፣ የኢራን ከቻይና እና ሩሲያ ጋር ያላት የንግድ እና የፖለቲካ ትስስር ግን ሳይበጠስ ቀጥሏል።
የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል ወደ መካከለኛው ምስራቅ ማዘንበል በምዕራብ ፓሲፊክ የነበራትን ወታደራዊ የበላይነት ክፍተት እንዲፈጠር ስላደረገው፣ ይህም የቻይናን እና የሩሲያን ስትራቴጂካዊ ስሌት እየቀየረ ይገኛል።
የጂኦፖለቲካ ባለሙያዎች እንደሚሉት በዚህ የስድስት ወራት የኃያላን ፍልሚያ ውስጥ ግልጽ አሸናፊ የሌለ ሲሆን፣ አሜሪካ እጅግ የላቀ ወታደራዊ የበላይነቷን ወደ ሙሉ ስትራቴጂካዊ እና ፖለቲካዊ ድል መተርጎም ሳትችል ስትቀር የኢራንም በጽናት መቆም ብቻውን ድል ሊባል አይችልም።
ይልቁንም ጦርነቱ የዓለም አቀፉን የኃይል ሚዛን፣ የደህንነት መዋቅር እና የጂኦ-ፖለቲካ ውድድር አዲስ የውጥረት ምዕራፍ ውስጥ የከተተ ሆኗል።
በሰለሞን ገዳ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: