ለዘመናት የውጭ ስንዴ ጫኝ መርከቦችን ከጂቡቲ ወደብ በጉጉት ስንጠብቅ የኖርንበት ያ የታሪክ ስብራት፣ ዛሬ በገዛ ማሳችን በበቀለ የመስኖ ስንዴ ተጠግኗል።
የዘመን መለወጫ ዋዜማ በሆነችው ጳጉሜን ወር መባቻ "የእመርታ ቀን" ተብሎ ሲሰየም ከስሙ ጀርባ ያለው ትልቁ ሀገራዊ ትርጉም ይሄው ከውድቀት ወደ ከፍታ የተደረገ ዝላይ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ሀገራችን ከምግብ ዋስትና ጥገኝነት ተላቃ ወደ ሙሉ የምግብ ሉዓላዊነት ያደረገችው ታሪካዊ ሽግግር የዚህ እመርታ ግንባር ቀደም ማሳያ ነው።
በዓለም አቀፍ የልማት ውይይቶች “የምግብ ዋስትና” እና “የምግብ ሉዓላዊነት” ሰፊ ሽፋን አላቸው። የምግብ ዋስትና በዋናነት ምግብ በማግኘት ላይ ብቻ ሲያተኩር (ምግቡ ከውጭ በዕርዳታ ወይም በብድር ቢመጣም)፣ የምግብ ሉዓላዊነት ግን ሕዝቦች የራሳቸውን የግብርና ፖሊሲ በነፃነት የመወሰን፣ የሀገር በቀል ምርትን የማሳደግና ከውጭ የእርዳታ ተፅዕኖ ሙሉ በሙሉ ነፃ የመሆን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መብትን ያመለክታል።
እ.ኤ.አ በ1981 ኢኮኖሚስቱ አማርቲያ ሴን በምርምሩ እንዳረጋገጠው፣ ርሃብ የሚከሰተው የምግብ አቅርቦት ስለታጣ ብቻ ሳይሆን የሕዝቦች የባለቤትነት መብትና የመንግሥታት መዋቅራዊ አሰራር ሲወድቅ ነው።
ኢትዮጵያም ለዘመናት የድርቅና የርሃብ ተምሳሌት ተደርጋ ስትገለጽ የቆየችው የተፈጥሮ ሀብት አጥታ ሳይሆን፣ የተሰጣትን ጸጋ ወደ ሕዝብ ጥቅም የሚቀይር የተገራ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፍልስፍና ባለመኖሩ ነበር።
ዛሬ ግን ይህ ታሪካዊ ስብራት በመደመር እሳቤ ወደማይቀለበስ የእመርታ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ ኢትዮጵያ በዓመት እስከ 1.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ከውጭ ለማስገባት ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ ታወጣ ነበር። አሁን ግን የበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት ስትራቴጂ ይህንን የጥገኝነት አዙሪት በጽኑ ሰብሮታል።
ከ3 ሺህ 500 ሄክታር በታች የነበረው የመስኖ ስንዴ ማሳ ወደ 3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ በማደግ አጠቃላይ የኢትዮጵያን የምግብ ፍላጎት ከማሟላት አልፎ ከ100 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ማስገኘት ተችሏል።
በተጨማሪም የሌማት ትሩፋት ንቅናቄ የወተት ምርትን ከ4.5 ቢሊዮን ሊትር ወደ 9 ቢሊዮን ሊትር በላይ በማሳደግ የፕሮቲን እጥረትና የሥነ-ምግብ ችግርን በዘላቂነት እየቀረፈ ይገኛል። የአቮካዶ እና የሆርቲካልቸር ኤክስፖርትም የውጭ ምንዛሪን በእጥፍ ሲያሳድግ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ያሳተፈው የከተማ ግብርና የኑሮ ውድነትን በማርገብ ላይ ነው።
የዚህ የልማት አብዮት ትልቁ ስኬት ምርትና የእህል ክምችት ብቻ ሳይሆን የተገኘው መንፈሳዊና ሥነ-ልቦናዊ ድልም ጭምር ነው። "እኛ ደሃ ነን፣ ሁልጊዜ እርዳታ እንፈልጋለን" የሚለውን የዘመናት የሥነ-ልቦና ስብራት አሽቀንጥሮ በመጣል በቦታው የ"እንችላለን" አሸናፊ መንፈስ እንዲተካ አድርጓል።
በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ውስጥ ምግብ ደሃ ሀገራትን የፖለቲካ ፍላጎት መጫኛ መሳሪያ ሆኖ ቢያገለግልም፣ ኢትዮጵያ ግን የምግብ ሉዓላዊነቷን በማረጋገጥ ይህንን የጂኦ-ፖለቲካ ጫና አክሽፋለች።
በቅርቡ ድርቅ በተከሰተባቸው ወቅቶች እንኳ ሀገራችን ያለምንም የውጭ እርዳታ የራሷን የሕልውና አቅም ተጠቅማ ዜጎቿን ከርሃብ መታደግ መቻሏ፣ ድርቅን ወደ ርሃብ የሚቀይረውን ታሪካዊ አዙሪት መበጠሷን ያመላክታል።
ዛሬ ጳጉሜን 1 የእመርታ ቀንን በምናከብርበት በዚህ ወቅት፣ የተጀመሩትን የስንዴ የመስኖ ልማት፣ የሌማት ትሩፋት፣ እና የከተማ ግብርና አጠናክሮ ማስቀጠል የሁላችንም ብሔራዊ ኃላፊነት ነው።
ሀገራችን ከርሃብ ተምሳሌትነት ወጥታ የአፍሪካ የእህል ጎተራ የመሆን ራዕይዋን በተግባር እያሳካች ነው። አዲሱ ዓመትም የላቀ የእመርታ ዘመን መሆኑ የማይቀር እውነታ ሆኗል።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: