የቻይናው የቴክኖሎጂ ግዙፍ ኩባንያ ኢሃንግ፣ በሆንግ ኮንግ ከተማ ያከናወነውና ሰው አልባ የኤሌክትሪክ አውሮፕላን ወይም "የበረራ ታክሲ" የበረራ ሙከራ በስኬት መጠናቀቁን ይፋ ማድረጉ የከተሞች የትራንስፖርት ታሪክ አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን ያበሰረ ሆኗል።
በሆንግ ኮንግ ሳይበርፖርት በተከናወነው የሙከራ በረራ፣ ኩባንያው በዘርፉ ቀዳሚ የሆነውንና "EH216-S" የተሰኘውን ዘመናዊ የበረራ ተሽከርካሪ ለዓለም ያስተዋወቀ ሲሆን፣ ተሽከርካሪው እንደ ሄሊኮፕተር ቀጥታ ተነስቶ ቀጥታ የማረፍ ልዩ የቴክኖሎጂ ብቃት የተላበሰ ነው።
በአንድ ጊዜ ሁለት መንገደኞችን የመያዝ አቅም ያለው እና እስከ 120 ሜትር ከፍታ ላይ የመብረር ችሎታ ያለው ይህ አዲስ የፈጠራ ውጤት፣ በአንድ የኤሌክትሪክ ቻርጅ ብቻ ለ30 ደቂቃዎች ያህል በአየር ላይ መቆየት እንደሚችል ተረጋግጧል።
ይህ የወደፊት የከተማ ትራንስፖርት ቴክኖሎጂ ቀደም ሲል በቻይና ትላልቅ ከተሞች ማለትም በጓንግዙ እና በሄፌይ ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ለከተማ ውስጥ አጭር ርቀት ትራንስፖርትና ለቱሪስት መስህብ ዕይታዎች ከፍተኛ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
የሆንግ ኮንግ አስተዳደር የከተማዋን የትራንስፖርት አማራጭ ለማዘመን "የዝቅተኛ ከፍታ ኢኮኖሚ" የተሰኘ ስትራቴጂ ነድፎ እየሰራ በሚገኝበት በዚህ ወቅት፣ የኢሃንግ ስኬታማ የሙከራ በረራ የዚሁ ታላቅ ምኞት አካልና የከተማዋን የትራንስፖርት ገጽታ የሚቀይር ትልቅ እመርታ ተደርጎ ተወስዷል።
ኢሃንግ ይህንን ፕሮጀክት ከኳን ቹንግ ስማርት ሞቢሊቲ እና ከሳይበርፖርት ጋር በመተባበር እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን፣ ዋና ዓላማውም በከተማዋ የዝቅተኛ ከፍታ በረራዎችን ይበልጥ ተደራሽ፣ አካባቢን የማይበክሉ እና ቀልጣፋ ማድረግ ነው።
በቅርብ ዓመታት ውስጥ በሆንግ ኮንግ ሰማይ ላይ በርካታ መሰል ሰው አልባ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለዕለታዊ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚሰማሩ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህም የዓለም ከተሞችን የትራፊክ እንግልት በመቀነስ ረገድ የራሱን ትልቅ ድርሻ ያበረክታል።
በላሉ ኢታላ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: