የኦሮሞ ሕዝብ መገለጫ የሆኑ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶችን በማጉላት ለሀገር አቀፍና ለዓለም አቀፍ ቱሪዝም መስህብነት መጠቀም እንደሚገባ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ጀሚላ ሲምቢሩ ገለጹ።
የክረምቱን መውጣትና የብርሃኑን አዲስ ዓመት መባቻ ተከትሎ በወጣት ሴቶችና ወንዶች ውብ ባህላዊ ክዋኔዎች የሚከበረው የጎቤና ሺኖዬ ፌስቲቫል በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
የበዓሉን መበሰር አስመልክቶ በተዘጋጀው መድረክ ላይ የተገኙት ቢሮ ኃላፊዋ መንግሥት እንዲህ ያሉ ሀገር በቀል ባህላዊ በዓላት እሴታቸውንና ይዘታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ እንዲሁም ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የጎቤና ሺኖዬ በዓል የኦሮሞን ጥንታዊ ባህል፣ ማህበራዊ ትስስርና ድንቅ እሴቶች በጠበቀ መልኩ የሚከናወን በመሆኑ፣ ወጣቶች ትውፊታቸውን የሚያውቁበት፣ አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበትና የማንነታቸውን ማህተም ለዓለም የሚያስተዋውቁበት ትልቅ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።
በዓሉ የወጣቶች የክረምቱን ማብቃት ማብሰሪያ ከመሆኑ ባሻገር፣ የኦሮሞን ሀብታም ባህላዊ ቅርሶች ለዓለም አቀፍ የቱሪዝም ገበያ ለማስተዋወቅና የኢኮኖሚ አቅም ለማሳደግ የሚደረገውን ሀገራዊ ጥረት በእጅጉ የሚያግዝ የኪነጥበብና የባህል እሴት እንደሆነ ተናግረዋል።
በሩት ወርቁ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: