የማዕድን ዘርፍ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በቂ አቅም፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና የተቀናጀ የመረጃ ሥርዓት ሳይገነባለት በመቆየቱ፣ ሀገራችን ከሰፊው የከርሰ ምድር ጸጋዋ ማግኘት የሚገባትን ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሳታገኝ ቆይታለች።
ይሁን እንጂ ዘርፉ በአዲሱ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ውስጥ ከተቀመጡት አምስት ዋና ዋና የምጣኔ ሀብት ምሰሶዎች አንዱ ሆኖ ከተለየ ወዲህ፣ ከጥሬ ሀብት አቅራቢነት አልፎ ወደ ስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ ሞተርነት እያደረገ ያለው መዋቅራዊ ሽግግር እጅግ አበረታች ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል።
ይህ የሪፎርም እርምጃ በተለይም በውጭ ምንዛሪ ግኝት እና በባንክ ክምችት ረገድ ታሪካዊ የሚባል እመርታን ይዞ መጥቷል።
የተወሰዱት የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎች ሕገ-ወጥ የኮንትሮባንድ ዝውውርን በመግታት፣ ባህላዊ እና ዘመናዊ አምራቾችን ወደ ሕጋዊ የባንክ ሥርዓት እንዲገቡ አድርገዋል።
ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ 44 ቶን የወርቅ ምርት ለብሔራዊ ባንክ ቀርቦ 5.7 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ሊገኝ ችሏል። ይህ ገቢ ወርቅ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቡና የላቀ ገቢ ያስገኘበት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ይህ አፈጻጸም የብሔራዊ ባንክን የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከማሳደግ ባለፈ፣ የጥቁር ገበያን መዛባት በማቃለል እና የኢትዮጵያን የብድር አስተማማኝነት በማሻሻል ለአጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት ትልቅ አቅም ሆኗል።
በተጨማሪም ሌሎች አምራች ዘርፎች የካፒታል ዕቃዎችን ከውጭ ለማስገባት የሚፈልጉትን የፋይናንስ አቅም በመፍጠር ረገድ የማይተካ ሚና ተጫውቷል።
ከውጭ ምንዛሪ ግኝት በተጓዳኝ ዘርፉ በተኪ ምርቶች አቅርቦት እና በእሴት ጭመራ እያስመዘገበ ያለው ለውጥ ሌላው የሪፎርሙ ትልቅ ስኬት ነው።
ኢትዮጵያ የማዕድን ሀብቷን በጥሬው ወደ ውጭ ከሚላክበት አሠራር በማላቀቅ የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን በግብዓት ለማስተሳሰር ሰፊ እንቅስቃሴ ጀምራለች።
ለዚህም በማሳያነት 5 የወርቅ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች፣ 5 የሴራሚክ ፋብሪካዎች፣ አንድ የተፈጥሮ ጋዝ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ እና የማዳበሪያ ፋብሪካ የመሠረተ ድንጋይ ተቀምጦላቸው ግንባታቸው በተፋጠነ ሁኔታ በመካሄድ ላይ ይገኛሉ። 12 የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በሥራ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ሌሎች አዳዲስ የሲሚንቶ ፕሮጀክቶች እየተሠሩ ናቸው፡፡
እነዚህ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የማዕድን ሀብትን እሴት ወደ ተጨመረበት ምርት በመቀየር በውጭ ምንዛሪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት፣ ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና የኢንዱስትሪውን ዘርፍ በጽኑ መሠረት ላይ ለማቆም የላቀ ፋይዳ አላቸው።
በቀጣይም ዘርፉ ለሀገራችን ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እጅግ የጎላ እንደሚሆን አሁን ላይ የተጀመሩት ተጨባጭ ሥራዎች ግልጽ ማሳያ ናቸው።
በ2019 ዓ.ም እና በሚቀጥሉት ዓመታት የማዕድን ዘርፉ የሀብት ፍለጋን፣ ምርትን እና ማቀነባበርን በማስተሳሰር የኢትዮጵያን የወደፊት የኢኮኖሚ መዋቅር የመቀየር ስትራቴጂካዊ ሚናውን አጠናክሮ ይቀጥላል።
ማዕድንን ከጥሬ ሀብትነት አልፎ የቴክኖሎጂ ሽግግር ማምጫ፣ የኢንዱስትሪ ትስስር መፍጠሪያ እና የዘላቂ ብልጽግና ማረጋገጫ ሞተር የማድረጉ ጉዞ በተጨባጭ ተግባራት ታጅቦ ወደ ተሻለ የዕድገት ምዕራፍ በመሸጋገር ላይ ይገኛል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: