የኢትዮጵያን ማንሠራራት የሚያመላክተው የጳጉሜን 1 የእመርታ ቀን ሀገራዊ መድረክ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት በይፋ ተከፍቷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ከፈተና ወደ ዕድል፣ ከጥገኝነት ወደ ራስን መቻል፣ ከተረጂነት ደግሞ ወደ አምራችነት ተሸጋግራለች።
በሁለንተናዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና በፋይናንስ ሥርዓት ዘመናዊነት ያስመዘገበችው መዋቅራዊ ስኬት ለኢንቨስትመንት እና ሀገር በቀል ሀብት ማሰባሰብ አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን አመላክተዋል።
በበጋ ስንዴ፣ በምግብ ሉዓላዊነትና በሌማት ትሩፋት የተመዘገቡት አኩሪ ውጤቶች የሀገራዊ ነጻነታችንና የጽናታችን ማረጋገጫዎች ናቸው ሲሉም አብራርተዋል።
በ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ እና በማዕድን ዘርፍ በተገኘው እመርታ የውጭ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉንና የኤክስፖርት ገቢ ማደጉን ጠቅሰዋል።
በገቢዎችና ጉምሩክ ዘርፍ የተዘረጉት የኢ-ፋይሊንግ እና የኢ-ፔይመንት ዲጂታል አሠራሮች አዲስ የታማኝነትና የቅልጥፍና ባህል መፍጠራቸውን አንስተው፣ አምራችነትን እንደ ዋና ዕሳቤ፣ ስልትና ግብ በመውሰድ እያንዳንዱ ተግባር ዕሴት የሚጨምር መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።
"ኢትዮጵያ እየተለወጠች፣ እያመረተችና እያንሠራራች ነው" መሆኑን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እመርታ የመጨረሻ መዳረሻ አይደለም፤ ወደ ከፍታ የሚያሻግረን መንገድ ነው ብለዋል።
በመሆኑም ዛሬ ያገኘነውን እመርታ ወደ ነገ ከፍታ ለመቀየር፣ የበለጠ መሥራት፣ የበለጠ ማምረት እና የበለጠ መፍጠር ይጠበቅብናል ሲሉም አስገንዝበዋል።
በአሸናፊ እንዳለ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: