Search

የቢሊዮን ዶላሮች ስኬት፡ የኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ እመርታ

ረቡዕ መስከረም 27, 2019 97

ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ከጥቂት ባህላዊ ዘርፎች አሠራር ተላቅቃ በብዙ ዘርፎች የተደገፈ ሰፊ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አድርጋለች።

በዚህ አዲስ የዕድገት አቅጣጫ ውስጥ ደግሞ የማዕድን ዘርፍ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከደገፉት አምስት ዋና ዋና ምሰሶዎች አንዱ ሆኖ ብቅ ብሏል።

ባለፉት አምስት ዓመታት ከተተገበሩ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ጀምሮ ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ወደ ተግባር በመቀየር በዘርፉ የተመዘገቡት ውጤቶች የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ያሳደጉ፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የሳቡ እና ለበርካታ ዜጎች አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን የፈጠሩ ሆነዋል።

ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ በሕዝብ ተወካዮች እና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 7ኛ የሥራ ዘመን 1ኛ ዓመት የጋራ መደበኛ ስብሰባ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ባለፉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የተወሰዱ የፖሊሲ እርምጃዎች ትልቅ አስተዋጽኦ ማሳረፋቸውን አብራርተዋል።

በተለይም የማዕድን ዘርፍ ልማትን ማስፋፋት የዚሁ የኢኮኖሚ እመርታ ዋና አካል መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ፣ በበጀት ዓመቱ የኢትዮጵያን አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ወደ 10.1 በመቶ ለማሳደግ የታቀደውን ቁልፍ ግብ ለማሳካት የማዕድን ዘርፉ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረው አስምረውበታል።

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ኢትዮጵያ ከማዕድን ወጪ ንግድ ከ 5.7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ችላለች።

በተለይም በዘመናዊ ኩባንያዎች እና በባህላዊ አምራቾች የተቀናጀ ጥረት 44 ቶን ወርቅ ማምረት የተቻለ ሲሆን፣ ይህም በኢትዮጵያ የወርቅ ምርት ታሪክ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ይዟል።

ከዚህ በተጨማሪ ለሲሚንቶ፣ ለብረት፣ ለሴራሚክስ እና ለጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ኃይል ማመንጫ የሚሆን የድንጋይ ከሰል ከውጭ ለማስገባት በየዓመቱ ይወጣ የነበረውን በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ለማስቀረት ሰፊ ሥራ ተከናውኗል።

የሀገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል ምርትን በማሳደግ የውጭ ምንዛሬ ብክነት ከፍተኛ በሆነ ሁኔታ እንዲቀንስ ተደርጓል።

ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጥሮ ጋዝ ማውጣት የጀመረች ሲሆን፣ ለማዳበሪያ እና ለብረት ማቅለጫ ፋብሪካዎች ግብዓት የሚሆኑ ምርቶች ወደ ሥራ መግባት ችለዋል።

በዚህ ዘርፍ በተከናወኑ የልማት እንቅስቃሴዎች ከ271 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኘው እና የአላይድ ጎልድ ኮርፖሬሽን አካል የሆነው የኩርሙክ ወርቅ ፋብሪካ የኢትዮጵያ ትልቁ እና ዘመናዊው የወርቅ ማምረቻ ተቋም ሆኖ ተገንብቷል።

ኩባንያው ከዓመታት የፍለጋ፣ የምህንድስና እና የግንባታ ሥራዎች በኋላ የመጀመሪያውን የሙከራ ምርት ለማምረት የሚያስችለውን የመጨረሻ ምዕራፍ የተግባር ሙከራ ማድረጉ የወርቅ ምርት መጠኑን በአስደናቂ ሁኔታ የሚጨምረው ከመሆኑም በላይ የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ አዲስ ማረጋገጫ ሆኗል።

በቀጣይ የበጀት ዓመት ከማዕድን ዘርፍ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ ወደ 6.7 ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የፔትሮሊየም፣ የተፈጥሮ ጋዝ፣ የብረት፣ የፖታሺየም እና የሊትየም ሀብቶች በሰፊው ወደ ማልማት ምዕራፍ ለማሸጋገር ዝግጅቶች ተጠናቅቀዋል።

የተፈጥሮ ጋዝ ምርትን ለትራንስፖርት፣ ለማዳበሪያ ምርት እና ለኃይል ማመንጫነት ለማዋል ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።

እንደ ፖታሽ ያሉ ለግብርና እና ለኢንዱስትሪ ወሳኝ የሆኑ ማዕድናትን በስፋት ወደ ምርት በማስገባት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞ የማፋጠን ሥራዎች ትልቅ ተስፋ ጥለዋል።

በሃና ምንዳሁን

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: