Search

የኢትዮጵያ መልህቅነት፡ አዲሱ የጂኦ-ፖለቲካ አቅጣጫ

ረቡዕ መስከረም 27, 2019 67

የኢትዮጵያ የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ዕይታ ለረጅም ጊዜ በህልውና መከላከያ እና በአጸፋዊ ምላሽ ላይ ተወስኖ መቆየቱ ይታወቃል።

ይሁን እንጂ አሁን እየተቀረጸ ያለው አዲሱ የጂኦ-ፖለቲካ ስሌት ይህንን የመከላከል እሳቤ በመቀየር ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦች እንደ መልህቅ ሀገር (Anchor State) ሥልጣኔዋን እና አቅሟን ወደምታሻግርበት ወሳኝ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።

ይህ ሽግግር ኢትዮጵያን ከተፅዕኖ ተቀባይነት እና ከአድማጭነት ወደ ቀጣናዊ ወሳኝነት የሚያመጣ ታሪካዊ እርምጃ ነው።

በመካከለኛው ምሥራቅ እና በቀይ ባሕር ቀጣና የተፈጠረው የኃያላን የጂኦ-ፖለቲካ ሽኩቻ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰበ በመጣበት በዚህ ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "ዝናብ ጣሪያ ለይቶ አይዘንብም" በማለት የገለጹት ነባራዊ እውነታ የኢትዮጵያን ስትራቴጂካዊ ንቃት የሚጠይቅ ነው።

የዓለም የንግድ እንቅስቃሴ የደም ሥር የሆነው የባብ አል-መንደብ ወሽመጥ የንግድ መተላለፊያ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ትኩሳት እና የውክልና ጦርነት ማዕከል በሆነበት ሁኔታ፣ የገቢ እና ወጪ ንግዷን ከ90 በመቶ በላይ በጅቡቲ ወደብ በኩል የምታሳልፈው፣ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት እና ኢኮኖሚዋ በፍጥነት እያደገ ያለችው ኢትዮጵያ ከዚህ ቀጣናዊ ንዝረት ርቃ በባዕዳን ስሌት ውስጥ ብቻ ተወስና ልትቀጥል አትችልም።

በቀይ ባሕር የሚዘንበው የፖለቲካ ዝናብ በቀጥታ የኢትዮጵያን ጣሪያ የሚያርስ በመሆኑ ሀገራችን በነባራዊ ሁኔታዋ ከባሕር ጠርዝ ገሸሽ እንድትል የተደረገችበትን የቆየ ስትራቴጂያዊ መልክዓ ምድር ቀይራ ብሔራዊ ጥቅሟን ማረጋገጥ ግዴታዋ ሆኗል።

በዚህ ውጫዊ ጫና እና ውስጣዊ አቅም መገናኛ ላይ የኢትዮጵያ የመልህቅነት (Anchor State) ሚና ትልቅ ትርጉም ይይዛል።

አንድ ሀገር አህጉራዊ ቁመና እና ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችለው በካርታ ላይ በሚታይ ግዝፈት፣ በታሪክ ወይም በሕዝብ ብዛት ብቻ አይደለም፤ ታሪክ፣ መልክዓ ምድር እና ተቋማትም የመገኛ አቅም ይፈጥራሉ።

ይሁንና ዘላቂ ቀጣናዊ ተፅዕኖ እና የመልህቅነት ሥፍራ የሚረጋገጠው ኢትዮጵያ ሌሎች ዋጋ የሚሰጡትን እና በቀላሉ ሊተኩት የማይችሉትን አቅም ለቀጠናው ስታቀርብ ነው።

ጠንካራው ጥያቄ ሌሎች ሀገራት ኢትዮጵያን እንዴት እንደሚቀበሏት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ለቀጣናው ምን ተግባራዊ እሴት ይዛ ትመጣለች የሚለው ነው።

ለዚህም ምላሹ የኃይል ትስስር፣ የአቪዬሽን እና ሎጂስቲክስ የበላይነት፣ የንግድ ኮሪደሮች፣ የገበያ ተደራሽነት እና በቀጣናው ውስጥ ያሉ የንግድ እና የሰዎች እንቅስቃሴ እንቅፋቶችን የሚቀንሱ ተመጋጋቢ የዲጂታል ሥርዓቶችን መዘርጋት ነው።

የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሚና፣ የአፍሪካ ሕብረት እና የኢጋድ ተቋማትን እንዲሁም የዘመናት የሽምግልና አቅምን በመጠቀም ሀገራትን በጋራ ቀጠናዊ ችግሮች ዙሪያ ማሰባሰብ የመልህቅነት ሚናዋ ዋነኛ መገለጫ ነው።

ይህ ማሰባሰብ ደግሞ በባዶ የፖለቲካ ንግርት ሳይሆን ወደ አምራች ገበያዎች፣ ወደ ዕውቀት እና ቴክኖሎጂ ትስስሮች፣ ወደ ጤና እና የአየር ንብረት ትብብር መቀየር ሲችል ኢትዮጵያ እውነተኛ የቀጣናው ምሰሶ ትሆናለች።

ለዚህም ነው በሙሉ አቅሙ ተጠናቅቆ ኃይል በማመንጨት ላይ የሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከብሔራዊ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትነቱ ባሻገር ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይልን በማስፋፋት ሱዳን፣ ጅቡቲ እና ኬንያን ጨምሮ ለጎረቤት ሀገራት ኤሌክትሪክ በማቅረብ እርስ በርስ የተሳሰረ የቀጣና የኃይል ሥርዓትን ለመፍጠር ያላትን ሰፊ ርዕይ የሚያሳየው።

ይህ የኢኮኖሚ መልክዓ ምድራዊ ትስስር ቀልጣፋ ኮሪደሮችን እና ድንበር ተሻጋሪ ግንኙነቶችን በማጠናከር በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስር የተቀናጀ ገበያን እውን ለማድረግ ያግዛል።

ከዚህም በተጨማሪ እንደ አረንጓዴ ዐሻራ ተነሳሽነት ያሉ ተግባራት ዛሬ ላይ ቀጣናዊ እና አህጉራዊ ጠቀሜታን አግኝተው ኢጋድ የኢትዮጵያ ጥረትን በማድነቅ ለCOP32 ፕሬዝዳንትነት ሙሉ ድጋፉን እስከ መስጠት አድርሶታል።

በዓለም አቀፍ መድረክም በ2024 የብሪክስ አባል መሆኗ ኢትዮጵያ ከዋና ዋና አዳጊ ሀገራት ጋር ያላትን ቁርኝት በማስፋት የዲፕሎማሲ አድማሷን ከአፍሪካ አልፎ ወደ እስያ፣ መካከለኛው ምሥራቅ፣ አውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ እንድትዘረጋ አስችሏታል።

ይህ ሁሉ እንቅስቃሴ የሚመራው በመደመር መንግሥት የውጭ ግንኙነት እሳቤ ሲሆን አቅጣጫውም የዜጎችን ጥቅም ማስቀደም፣ ከጎረቤቶች ጋር ሰላም መፍጠር፣ ክልላዊ ትስስርን ማጠናከር እና ዓለም አቀፍ አጋርነትን ማስፋፋት በሚሉ አራት የትኩረት ማዕዘናት ላይ የቆመ ነው።

ይህ አካሄድ ንቁ አማራጭ፣ ከሁኔታዎች ጋር የሚላመድ እና አጀንዳ ቀራጭ በሚሉ መርሆች የሚመዘን ነው።

ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር የምትገነባው የተረጋጋ ግንኙነት ብሔራዊ ደኅንነቷን ሲደግፍ ቀጣናዊ ትስስሩ ገበያዋን ያሰፋል፤ ዓለም አቀፍ ሽርክናው ደግሞ ለኢንቨስትመንት እና ቴክኖሎጂ በሮችን ይከፍታል።

ስለሆነም ኢትዮጵያ ተነሳሽነቱን በመውሰድ፣ የውጭ ጫናን በመቋቋም፣ ሁኔታዎች ሲለዋወጡ አቅጣጫዎችን በማስተካከል እና ሀገራዊ አቅጣጫዋን በገዛ ዜጎቿ ፍላጎት በመወሰን የወሰን አወቃቀሯን ጠንካራ አድርጋ ትጠብቃለች።

የአፍሪካ ቀንድ መልህቅ መሆን ማለት የሀገርን የውስጥ አቅም ወደ ቀጣናዊ እሴት፣ ቀጣናዊ ተሳትፎን ደግሞ ወደ ሰፊ ዓለም አቀፋዊ አጋርነት የመቀየር ጥበብ ነው።

የኢትዮጵያ የመልህቅነት መለኪያም በካርታ ላይ ምን ያህል በግልጽ እንደምትታይ ወይም በሕዝቧ ቁጥር ብዛት ሳይሆን በዙሪያዋ ለሚገኙ ሀገራት ምን ያህል መረጋጋትን፣ ትስስርን እና የጋራ የብልጽግና ዕድልን ማሰባሰብ እንደቻለች የሚረጋገጥበት እውነት ነው።

ከህልውና ሥጋት ንግርት ወጥታ፣ ራሷን አግዝፋ፣ አጀንዳ ቀርጻ ቀጣናውን የምትመራበት ይህ የጂኦ-ፖለቲካዊ ሽግግር የኢትዮጵያን አዲስ ታላቅነት በተግባር የሚያሳይ ነው።

በበረከት ሽመልስ

#የመደመርመንግሥት

#ትልቅ_ሀገር! #ትልቅ_ሕዝብ! #ታላቅ_ርዕይ!

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: