የኢትዮጵያንና የየሀገራቸውን ሁለንተናዊ የትብብር አድማስ በማስፋት የዲፕሎማሲ ግንኙነትን ለማጎልበት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ በኢትዮጵያ አዲስ የተሾሙ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ገለጹ።
ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ከአፍሪካ፣ እስያ፣ መካከለኛው ምሥራቅ፣ አውሮፓ እና ካሪቢያን ሀገራት በኢትዮጵያ አዲስ የተሾሙ የ16 ሀገራት አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ በትናንትናው ዕለት ተቀብለዋል።
በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በክብር ዘብና በማርሽ ባንድ ደማቅ ሥነ ሥርዓት ታጅቦ በተካሄደው መርሐ ግብር፤ በኢትዮጵያ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች፣ የሰሜን ኮሪያ፣ የቆጵሮስ፣ የቼክ ሪፐብሊክ እና የአየርላንድ አምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤያቸውን ለፕሬዚዳንቱ አቅርበዋል።
በተጨማሪም የሕንድ፣ የቻድ ሪፐብሊክ፣ የኦስትሪያ፣ የኖርዌይ፣ የፊንላንድ ሪፐብሊክ፣ የማልታ ሪፐብሊክ፣ የጣሊያን፣ የባርቤዶስ፣ የደቡብ ኮሪያ፣ የሉክሰምበርግና የግሬናዳ አምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤያቸውን አስረክበዋል።
አምባሳደሮቹ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያንና የየሀገራቸውን ሁለንተናዊ የዲፕሎማሲ ትብብርና ግንኙነት በማጠናከር የጋራ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት ይሰራሉ።
በኢትዮጵያ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች አምባሳደር አብደላ ሀሰን ኡባይድ ሀሰን አልሻምሲ በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ጥልቅ ወዳጅነት የገነቡ ስትራቴጂካዊ አጋር ሀገራት መሆናቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የሀገራቸው አምባሳደር ሆነው በመሾማቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው የጠቀሱት አምባሳደሩ፣ በቆይታቸው የሀገራቱን የትብብር ብሩህ አድማስ በማስፋት የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብት ጠንካራ ግንኙነት ለመገንባት በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የቆጵሮስ አምባሳደር ሳቫስ ቪላድሚሩ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የቆጵሮስ አምባሳደር ሆነው በመሾማቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል። በቀጣይም በኢትዮጵያና በቆጵሮስ መካከል የባህል፣ የንግድና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን በማጎልበት የሀገራቱን ኢንቨስትመንት ለማጠናከር በልዩ ትኩረት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያና በቼክ ሪፐብሊክ መካከል በመንግሥት ለመንግሥትና በሌሎች ዘርፎች ጠንካራ የዲፕሎማሲ ትብብር እየተገነባ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ያን ሮቼክ ናቸው።
የሀገራቱን ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነትም በተለያዩ የኢንቨስትመንትና የፕሮጀክት ግንባታ ትብብር የበለጠ ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰሩ አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ የአየርላንድ አምባሳደር ኪያራን ማደን በበኩላቸው፤ ለተሰጣቸው ሹመትና ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይም የኢትዮጵያን ፈጣን ዕድገት በመደገፍ የአየርላንድ አልሚ ባለሀብቶች በተለያዩ የንግድና ኢንቨስትመንት አማራጮች የሚሰማሩበትን ሁኔታ ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም በቅርቡ የሀገራቱን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር በባህል ዘርፍ ላይ ያተኮረ ሁነት ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውሰዋል።
በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር ዴቪሽ ዑታም በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያንና የሕንድን ታሪካዊና ጠንካራ የዲፕሎማሲ ወዳጅነት የበለጠ ለማጎልበት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያን ፈጣንና አስደናቂ ዕድገት የሚያሳልጥ የንግድና ኢንቨስትመንት የኢኮኖሚ ትብብርን ለማጎልበት እንደሚሰሩ የተናገሩት ደግሞ በኢትዮጵያ የኦስትሪያ አምባሳደር ፒተር ኤልስነርማካይ መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: