Search

ከከርሰ ምድር ሀብትነት ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ አቅም

ረቡዕ መስከረም 27, 2019 79

ኢትዮጵያ በከርሰ ምድሯ አቅፋ የያዘቻቸውን በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች ሳትጠቀምባቸው ለዘመናት ቆይታለች።

አሁን ላይ ግን የመደመር መንግሥት ለተፈጥሮ ሀብት ልማት በሰጠው ልዩ ትኩረት ይህ ታሪክ በእጅጉ እየተቀየረ ይገኛል።

ለአብነትም የሀገራችን የወርቅ ማዕድን በአሁኑ ወቅት ለሀገራችን የውጭ ምንዛሬ ገቢ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ኢኮኖሚያዊ አቅም ጉልህ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት እንደ ወርቅ፣ ታንታለም፣ አይረን ኦር እና ሊቲየም ያሉ ማዕድናት ከፍተኛ ክምችት ቢኖራቸውም በአግባቡ ሳይጠቀሙባቸው ለረጅም ጊዜ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኝ፣ የማዕድን ዘርፉን ከኢኮኖሚው ዋና ምሰሶዎች አንዱ ለማድረግ በተወሰዱ የፖሊሲ እና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች፣ የወርቅ ምርት እና ገቢ እየጨመረ መምጣቱን ገልዋል።

በ2014 ዓ.ም ከ500 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ብቻ የነበረው የማዕድን ምርት ኤክስፖርት ገቢ አሁን ወደ 5.7 ቢሊዮን ዶላር ማደጉን በማሳያነት ጠቅሰዋል። ለዚህ ለውጥ ደግሞ የአንበሳውን ድርሻ ያበረከተው የወርቅ ምርት ነው።

በ2018 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ 44 ቶን የወርቅ ምርት ወደ ዓለም ገበያ በመላክ 5.65 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷ የወርቅ ዘርፉ ለሀገራችን የውጭ ምንዛሬ ግኝት የሚጫወተውን ቁልፍ ሚና ያሳያል።

የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያ፣ የብሔራዊ ባንክ የወርቅ ግዢ ማበረታቻ፣ የሕገወጥ ማዕድን ምርት ቁጥጥር እና የባህላዊ ወርቅ አምራቾች ወደ መደበኛ ሥርዓት መግባት አመርቂ ውጤት ለመምጣቱ ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው።

“ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ወዲህ 44 ቶን ወርቅ ማምረት መቻሉ በራሱ ምን ያህል ማምረት እንደምንችል የሚያመላክት ነው፤ ይህን ያመጣው ግን በዋናነት ፖሊሲው ነው” ብለዋል ኢንጅነር ሀብታሙ።

የወርቅ ምርትን ወደ ትልቅ የኢንዱስትሪ ምርት ለማሸጋገር እየተገነቡ ካሉ ፕሮጀክቶች መካከል የኩርሙክ የወርቅ ፋብሪካ አንዱ ነው። ይህም ለረጅም ጊዜ በምድር ውስጥ ተቀብሮ የቆየ ሀብትን ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚቀይር ተጨማሪ አቅም እንደሆነ አመልክተዋል።

የማዕድን ዘርፉ ቀደም ሲል ከኢኮኖሚው የተነጠለ እንደነበር ያነሱት ደግሞ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢጃራ ተስፋዬ ናቸው።

የማዕድን ሀብትን በተመለከተ ለ60 ዓመታት የተሰበሰቡ ከ20 ሺህ በላይ ካርታዎች፣ ሪፖርቶችና መጻሕፍት በማደራጀትና በዲጂታል መልክ በማቅረብ ለኢንቨስተሮች ግብዓት እንዲሆኑ ተደርገዋል።

ይህም ወርቅን ጨምሮ የሀገራችንን እምቅ የማዕድን አቅም በሳይንሳዊ መረጃ ላይ ተመስርቶ ለመጠቀም የሚያግዝ ነው።

የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብስራት ከበደ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ከኢኮኖሚ ማሻሻያው በፊት የማዕድን ዘርፉ ለጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያደርግ የነበረው አስተዋጽኦ 0.8 በመቶ ያህል ብቻ እንደነበር ጠቅሰዋል።

የወርቅና ሌሎች ማዕድናት አቅምን በአግባቡ መጠቀም የሀገራችንን ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ያስረዳሉ።

የማዕድን ዘርፉ ጥሬ ሀብት አምርቶ ከመላክ ባሻገር እሴት ወደ መጨመር እንዲሸጋገር በትኩረት እየተሠራ መሆኑም ተገልጿል።

በኢንቲሃድ አብራር

#ትልቅ_ሀገር! #ትልቅ_ሕዝብ! #ታላቅ_ርዕይ!

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: