Search

የመደመር መንግሥት፦ የዲፕሎማሲ ተሰሚነት እና የመከላከያ አቅም ግንባታ

ዓርብ መስከረም 29, 2019 65

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በውስጥ ፈተናዎች እና በውጭ ጫናዎች መካከል የሀገራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ፣ የዲፕሎማሲ ተሰሚነቷን ለማሳደግ እና የመከላከያ አቅሟን ለማጠናከር የተለያዩ ሪፎርሞችን እና ሀገራዊ ተግባራትን ስታከናውን ቆይታለች።

በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ያላት ስትራቴጂያዊ አቀማመጥ፣ ከ130 ሚሊዮን በላይ የሕዝብ ቁጥሯ፣ የቀጣናዊ ሰላም ሚናዋ እና የተለያዩ የኢኮኖሚ አቅሞቿ ለዓለም አቀፍ ትብብር እና ዲፕሎማሲያዊ ትኩረት ወሳኝ መሠረት ሆነዋል።

የመደመር እሳቤ የሀገራችንን ችግሮች በራስ አቅም፣ በተቋማዊ ግንባታ፣ በምክክር እና በትብብር ለመፍታት ከሚያበረታቱ አቅጣጫዎች አንዱ ሆኗል። በዚህ ሂደት ኢትዮጵያ የታላቁን የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በራሷ አቅም ወደ ፍጻሜ ማድረሷ፣ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን የማስፈጸም አቅሟን ከማሳየት ባለፈ በዓባይ ውኃ ሀብት ላይ የፍትሐዊ አጠቃቀም እና የጋራ ተጠቃሚነት ጥያቄዋን በዓለም አቀፍ መድረክ እንድታስቀጥል አስችሏታል።

የሀገራችን ዲፕሎማሲ በተመሳሳይ ጊዜ በቀጣናዊ ሰላም፣ የኢኮኖሚ ትብብር፣ የኢንቨስትመንት እና የስትራቴጂያዊ ግንኙነቶች ላይ ትኩረት ሰጥቷል። ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ በአፍሪካ ኅብረት እና በሌሎች ዓለም አቀፍ መድረኮች ያላት ሚናም ለቀጣናዊ ጉዳዮች መፍትሔ ፍለጋ አስፈላጊ ሆኖ ቀጥሏል።

የመደመር መንግሥት የዲፕሎማሲ አቅጣጫ የሀገራችንን ጥቅም በማስቀደም ከተለያዩ ወገኖች ጋር ሚዛናዊ ግንኙነት መፍጠርን ያጎላል። ኢትዮጵያ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ጋር ወዳጅነት በመመሥረት፣ የጋራ ጥቅም የሚያስገኙ የንግድ እና የትብብር ዕድሎችን ማስፋት እንዳለባትም ያስገነዝባል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ “ኢትዮጵያ አጀንዳ ተቀባይ ከመሆን ወጥታ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች አጀንዳ ሰጪ መሆን አለባት” በማለት የሀገራችን የዲፕሎማሲ ተሳትፎ ከተከታይነት ወደ ንቁ ተሳትፎ እና አጀንዳ ቀራጭነት መሸጋገር እንዳለበት ያመለክታሉ።

በዚህ የዲፕሎማሲ ጉዞ ውስጥ የመከላከያ ኃይል ግንባታ የሀገራችንን ሉዓላዊነት እና ደኅንነት ለማስጠበቅ ከሚያስፈልጉ ዋና ዋና መሠረቶች አንዱ ነው። በአፍሪካ ቀንድ የሚታዩ የጸጥታ ችግሮች፣ የጽንፈኛ ቡድኖች እንቅስቃሴና በቀይ ባሕር የሚከሰቱ የደኅንነት ሥጋቶች ጠንካራ፣ ዘመናዊና ሙያዊ የመከላከያ ተቋም መኖሩን የበለጠ አስፈላጊ አድርገውታል።

ባለፉት ዓመታት የመከላከያ ሪፎርሙ የሰው ኃይል ሙያዊ ብቃትን፣ የዘመናዊ መሣሪያዎችን አጠቃቀም፣ የቴክኖሎጂ አቅምንና የተቋማዊ አደረጃጀትን ማሻሻል ላይ ትኩረት ሰጥቷል። የኢትዮጵያ አየር ኃይል በዘመናዊ የአየር መከላከያና የውጊያ አቅም ማሳደግ ላይ ያደረገው ሥራ፣ የምድር ጦር የሥራ አቅምን ማጠናከር እና የልዩ ዘመቻ አደረጃጀቶችን ማሳደግ የሪፎርሙ አካላት ናቸው።

የተዋጊ ጀቶች እና ዘመናዊ የድሮን ቴክኖሎጂዎች በወታደራዊ አቅም ግንባታ ዙሪያ በሚነሡ ውይይቶች ውስጥ ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ የመሣሪያዎች ግዥ እና አጠቃቀም ከሙያዊ ሥልጠና፣ ከጥገና አቅም እና ከተቋማዊ ቁጥጥር ጋር በግልጽ የሚታይ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የመረጃ ደኅንነት፣ የራዳር አቅም፣ የጸረ አየር መከላከያና የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም የዘመናዊ መከላከያ አሠራር ወሳኝ ክፍሎች ናቸው።

የሳይበር ደኅንነትና የመረጃ ቴክኖሎጂ አቅም ማሳደግም የሀገራችንን ስትራቴጂያዊ ተቋማት እና ወሳኝ መሠረተ ልማቶች ከዘመናዊ ሥጋቶች ለመጠበቅ ያለውን ጠቀሜታ ያሳያል። የባሕር ኃይል ግንባታ ጥረትም ከሀገራችን የባሕር በር ፍላጎት፣ ከቀይ ባሕር ደኅንነትና ከቀጣናዊ ትብብር ጋር የተያያዘ ስትራቴጂያዊ ጉዳይ ነው።

የመከላከያ ተቋም ጥንካሬ የሚለካው በመሣሪያ ብዛት ብቻ ሳይሆን በሙያዊ ብቃት፣ በተቋማዊ ታማኝነት፣ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መሠረት በሚያከናውነው ተግባርና የሕዝብን ደኅንነት በማስጠበቅ ባለው ብቃት ጭምር ነው። በዚህ መሠረት የመከላከያ ሪፎርሙ የሀገራችንን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ ባለፈ በቀጣናው የሚኖረውን የሰላምና የደኅንነት ሚና ለማጠናከር የሚያግዝ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ተሰሚነትና የመከላከያ አቅም ዕድገት እርስ በርስ የሚደጋገፉ ጉዳዮች ናቸው። የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች የሀገራችንን ጥቅም በሰላማዊ መንገድ ለማስጠበቅ ዕድል ሲፈጥሩ፣ ጠንካራና ሙያዊ የመከላከያ ተቋም ደግሞ ሉዓላዊነትንና ደኅንነትን ለማስጠበቅ ያስችላል። ይህ ጥምረት ኢትዮጵያ በቀጣናዊና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የሚኖራትን ተሳትፎ ለማጠናከር ወሳኝ ነው።

በቀጣዮቹ አምስት ዓታት የሀገራችንን የዲፕሎማሲ ተሰሚነት ማስፋት፣ የመከላከያ ኃይሉን በቴክኖሎጂና በሙያዊ ብቃት ማጠናከር፣ በቀጣናው የሰላም ግንባታ ያላትን ሚና ማሳደግና የባሕር በር ጥያቄዋን በሰላማዊ ውይይት ማስቀጠል ቁልፍ የትኩረት መስኮች ናቸው። የሀገራችን የወደፊት ጉዞ የሚወሰነውም ያሉትን አቅሞች በማጠናከር፣ የውስጥ ፈተናዎችን በሰላምና በምክክር በመፍታት እና ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር የጋራ ጥቅም የሚያስገኙ ግንኙነቶችን በማስፋት ላይ ነው።

በኢንቲሃድ አብራር

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: