Search

በካይሮ ከንቱ ሩጫ የማይገታው የኢትዮጵያ ልማት

እሑድ ጥቅምት 01, 2019 48

የግብጽ ባለሥልጣናት ከዓባይ እና ቀይ ባሕር አካባቢ ኢትዮጵያን ለማግለል የሚያካሂዱት የቀቢፀ ተስፋ ጉዞ፣ ጊዜው ያለፈበትን የቅኝ ግዛት ዘመን የበላይነት ቅዠት ለማስቀጠል የሚደረግ ከንቱ ጥረት ነው።

የግብጽ መሪዎች በቢልዮን የሚቆጠር ዶላር እያባከኑ በተለያዩ አህጉራት እየዞሩ የሚያሰሙት ስሞታ እና ምፅዋት ፍለጋ በደጅ ያለውን አፍሪካዊ መፍትሔ ንቆ የመተው እና ለአህጉራዊ ተቋማት ያላቸውን ዝቅተኛ ግምት በግልጽ ያሳያል።

ለርካታ ዓመታት በአንድ ወገን የበላይነት እና በራስ ወዳድነት ላይ የተገነባው የካይሮ ዲፕሎማሲ አፍሪካውያን በጋራ የመልማት እና የራሳቸውን ችግር በራሳቸው የመፍታት አቅም ላይ መድረሳቸውን መገንዘብ አልቻለም።

ኢትዮጵያን ከልማቷ ለማስተጓጎል እና የፍትሐዊ ውኃ አጠቃቀም ጥያቄዋን ለማደናቀፍ የሚደረገው ይህ ሩጫ የዓለም አቀፉን እና የቀጣናውን የኃይል ሚዛን መለወጥ ካለመቀበል የሚመነጭ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኪሣራ ማሳያ ነው።

የሚገርመው የግብጽ ባለሥልጣናት ኢትዮጵያን በምቀኝነት ስም በማጠልሸት ላይ ጊዜያቸውን ሲያባክኑ በገዛ ደጃቸው የተደቀነባቸውን እውነተኛ የኢኮኖሚ ውድቀት እና የቀይ ባሕር የደኅንነት ቀውስ ማየት አለመቻላቸው ነው።

በቀይ ባሕር ላይ በተፈጠረው የደኅንነት መታወክ እና በባብ ኤል-መንደብ በተካሄዱት ጥቃቶች ምክንያት የስዊዝ ቦይ የመርከቦች እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።

ይኸው የደኅንነት ቀውስ በግብጽ ኢኮኖሚ ላይ ያደረሰው ጉዳት በይፋዊ መረጃዎች የተረጋገጠ ሲሆን፤ ከእ.አ.አ 2022 እስከ 2023 የነበረው 10.25 ቢሊዮን ዶላር የነበረው የስዊዝ ቦይ ገቢ ወደ 3.99 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ብሏል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ መለወጥ እንቅልፍ ያሳጣት ግብጽ በወር እስከ 700 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በቋሚነት እያጣች መሆኑን የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) እና ሌሎችም ይፋዊ መረጃዎች ያረጋግጣሉ።

የኢትዮጵያ ልማት የእግር እሳት የሚሆንባት ካይሮ ግን ትክክለኛውን የደኅንነት ስጋት ከመዋጋት ይልቅ ትኩረቷን ኢትዮጵያ ላይ ማድረጓ የዲፕሎማሲ ድክመቷን ያጋለጠ ነው።

ዛሬ ጊዜው በከፍተኛ ሁኔታ ተቀይሯል፤ የካይሮ ጊዜ ያለፈበት የዛቻ እና የሽንገላ አካሄድ የሚሠራበት ዘመን ላይ አይደለንም።

እ.አ.አ በ2024 የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (CFA) በይፋ ወደ ሥራ መግባቱ እና ቋሚው የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን (NRBC) መቋቋሙ ወረቀት ላይ ብቻ ተወስኖ የነበረውን የቅኝ ግዛት ዘመን የውኃ ክፍፍል የመዝገብ ቤት የታሪክ ሰነድ ብቻ ማድረጉን አረጋግጧል።

ኢትዮጵያ የምትከተለው መርሕ ግልጽ ነው፤ አቋሟ ራሷ በመልማት የዜጎቿን ሕይወት መቀየር እንጂ ማንም ላይ ጉዳት ማድረስ አይደለም።

በዚህም ምክንያት የትኛውም የካይሮ ጫና ኢትዮጵያን ከዓባይ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትም ሆነ ከቀይ ባሕር ፍትሐዊ የባሕር በር ጥያቄዋ ሊያስተጓጉላት አይችልም።

ለግብጽ ብቸኛው እና ጠቃሚው አማራጭ ከአህጉሩ ውጭ እየዞሩ መማጸኑን ሳይሆን በሰጥቶ መቀበል መርሕ መሠረት ከኢትዮጵያ ጋር በቀጥታ መወያየት እና ወደ ናይል ተፋሰስ ሀገራት የጋራ ማዕቀፍ መመለስ ብቻ ነው።

ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በነበሩ ፈተናዎች አልፋ የቆመች፣ ዛሬ ደግሞ የዲፕሎማሲ እና በደኅንነት አጋርነቷ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነትን ያገኘች ጠንካራ ሀገር ነች።

ከ86 በመቶ በላይ የሚሆነውን የዓባይ ውኃ የምታመነጨው እና በቀይ ባሕር ደጅ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን በማንም ጫና አሰልፋ የማትሰጥ መሆኗን በሕዳሴው ግድብም ሆነ በሌሎች መዋቅራዊ ስኬቶቿ ለዓለም አረጋግጣለች።

የቀጣናው አዲስ ምዕራፍ እየተገነባ ያለው በጋራ ተጠቃሚነት፣ በነፃነት እና በፍትሐዊነት መሠረት ላይ በመሆኑ፣ የግብጽ ምቀኝነት እና ከንቱ ሩጫ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጉዞ ሊያስቆመው አያችለም።

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: