Search

ጥሬ ሀብትን ወደ እሴት፡ የኢትዮጵያ የወርቅ እና ማዕድን ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ

እሑድ ጥቅምት 01, 2019 83

ኢትዮጵያ በከርሰ ምድሯ በርካታ ያልተነኩ ውድ የተፈጥሮ ሀብቶችን ይዛ የምትገኝ ሀገር ነች።

ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ባሉ ሰፋፊ ቀጣናዎች ሥር የሚገኙት የወርቅ፣ የከበሩ ድንጋዮች፣ የብረት፣ የታንታለም፣ የሊቲየም እና የፖታሽ ክምችቶች የዚህ ታላቅ በረከት ማሳያዎች ናቸው።

ላለፉት በርካታ ዘመናት ይህንን የተፈጥሮ ጸጋ በባህላዊ ማውጣት ዘዴዎች ብቻ በመጠቀም ዘርፉ ሊሰጥ የሚችለውን ያህል ጥቅም ሳናገኝበት ቆይተናል።

አሁን ላይ ግን የተወሰዱ የፖሊሲ እና የአሠራር ማሻሻያዎች ዘርፉን አዲስ ወደሆነ የኢኮኖሚ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ዋና የልማት ምሶሶ እያደረጉት ይገኛሉ።

የማዕድን ዘርፉ ትልቁ መዋቅራዊ ሽግግር የሚጀምረው ከፖሊሲ አቅጣጫ ለውጥ ነው። ቀደም ሲል ጥሬ ወርቅን እና ሌሎች ማዕድናትን ያለ ምንም ተጨማሪ እሴት በቀጥታ ወደ ውጭ መላክ የተለመደ አሠራር ነበር።

ይህም ኢትዮጵያ ማግኘት የሚገባትን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና ከዘርፉ የምታገኘውን ዋጋ እንድታጣ አድርጓታል።

አሁን የተያዘው ስትራቴጂያዊ አቅጣጫ ግን ጥሬ ሀብትን በቀጥታ ከመሸጥ ይልቅ በሀገር ውስጥ የማጣራት፣ እሴት የመጨመር እና ምርቶቹን ወደ ተጠናቀቁ የኢንዱስትሪ ውጤቶች የመቀየር ግብ ላይ ያተኮረ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ ሥራ ያስጀመሩት የቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ የዚህ አዲስ ሀገራዊ አቅጣጫ ግልጽ ማሳያ ነው።

ይህ ታላቅ የኢንዱስትሪ አቅም የተፈጥሮ ሀብትን ከዘመናዊ ማኑፋክቸሪንግ ጋር በማስተሳሰር የወጪ ንግድ ገቢን ለማሳደግ፣ ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና የሀገር ውስጥ የጌጣጌጥ ኢንዱስትሪን መሠረት ለማጠናከር አልሞ የተገነባ ነው።

ይህም ግልጽ እና ተወዳዳሪ የሆነ የወርቅ እሴት ሰንሰለት በመገንባት ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን ማረጋገጫ ነው።

ከማዕድን ማውጣት እስከ ኤክስፖርት ድረስ ያለው ይህ አጠቃላይ የላቀ እሴት የመፍጠር ሂደት ኢትዮጵያን በምሥራቅ አፍሪካ የቀጣናው ዋና የማዕድን ማጣሪያ እና የንግድ ማዕከል የማድረግ ሰፊ ራዕይ አካል ነው።

አሠራሩ የውጭ ምንዛሬ ገቢን ከማሳደጉ ባሻገር ቀደም ሲል በኮንትሮባንድ እና በሕገ-ወጥ ንግድ መስመር ይባክን የነበረውን አቅም ወደ ሕጋዊ እና ግልጽ የፋይናንስ ሥርዓት በማስገባት የተፈጥሮ ሀብቱን ለትውልድ የሚሻገር ዘላቂ የኢኮኖሚ ጉልበት ያደርገዋል።

#የመደመርመንግሥት

በሔዋን ጌታቸው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: