Search

“ግብፅ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዳታገኝ ለመከላከል ምንም ዓይነት ሕጋዊ መብት የላትም”፦ ቲቦር ናዥ

ማክሰኞ ጥቅምት 03, 2019 73

ኢትዮጵያ የጀመረችውን ሀገራዊ ምክክር ውጤታማ በማድረግ እውነተኛ ብሔራዊ እርቅ መፍጠርና የውስጥ አንድነቷን ማጠናከር ከቻለች፣ የአፍሪካ ቁልፍና ታላቅ ሀገር መሆኗን ዳግም ማረጋገጥና ማስቀጠል እንደምትችል የቀድሞው የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲቦር ናዥ ገለጹ።

ዲፕሎማቱ ከኢቲቪ "አዲስ ዳያሎግ" ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቆይታ ስለ ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ፣ የጂኦፖለቲካ ጫናዎች እና የግብፅን የውጭ ግንኙነት አካሄድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ ወደብ አልባ በመሆኗ ከ90 በመቶ በላይ የወጭ ንግድ በአሁኑ ወቅት የንግድ መዳረሻዎቿ በአብዛኛው በጅቡቲ ወደብ ላይ ብቻ የተመሠረቱ መሆናቸውን ያነሱት ቲቦር ናዥ፤ በመሆኑም ተጨማሪ የባሕር በር የማግኘት አስቸኳይ ፍላጎት እንዳላትና የንግድ መዳረሻዎቿን ማስፋት እንደሚኖርባት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሕግ ማዕቀፍ ድጋፍ ያለውን የባሕር በር ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ፣ በድርድር፣ በስምምነት ወይም በረጅም ጊዜ ውል መፈጸም እንደምትፈልግ በግልጽ ማስታወቋን ጠቁመዋል።

ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ሀገር የባሕር በር ባለቤት መሆኗ ለውጭ ንግድ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናዊ ደህንነት እና የኢኮኖሚ ትስስር አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

ግብጽ እና አንዳንድ ሀገራት  ምንም ዓይነት የጋራ ዓላማ ሳይኖራቸው፣ ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር እንዳትጠጋና የባሕር በር ባለቤት እንዳትሆን እየተጣጣሩ እንደሚገኙ ያመላከቱት ዲፕሎማቱ፤ ግብፅ  ጫና ለመፍጠር እየሠራች መሆኑን አብራርተዋል።

በአገራቱ መካከል ጠንካራ የጋራ መግባባት እንደሌለና ያገናኛቸው ብቸኛ ነገር ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ቅሬታ መሆኑን የገለጹት ቲቦር ናዥ፣ ግብፅ ይህንን ሁኔታ በራሷ የጂኦፖለቲካ ጥቅም ለማዋል እየጣረች መሆኗን አንስተዋል።

"ግብፅ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዳታገኝ ለመከላከል ምንም ዓይነት ሕጋዊ መብት የላትም" ያሉት ዲፕሎማቱ፤ ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር በቅርብ ርቀት የምትገኝ ሀገር ብትሆንም ግብፅ ግን "የቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ ያሉ አገራት ብቻ ናቸው በባሕሩ ላይ መብት ያላቸው" በማለት የያዘችው አቋም ፍጹም ግብዝነት መሆኑን አጋልጠዋል።

ከ86 በመቶ በላይ የዓባይ ውኃ ምንጭ ኢትዮጵያ ሆና ሳለ ለዓባይ ምንም የማታበረክተው ካይሮ፣ ውኃው የሚነሳው ከኢትዮጵያ መሆኑን እንደምትዘነጋና ግብፅ በወንዙ ላይ የውኃ ጠብታ እንኳን ሳታስገባ የራሷን የውኃ ፍላጎት ለማስጠበቅ የምትከተለው አካሄድ ከባድ ቅራኔ ያለበት መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ብዙ ክፍሎች ያሉት አንድ ትልቅ ቤት መሆኗን የገለጹት ዲፕሎማቱ፣ ነዋሪዎቿ ቤቱን በጋራ የመጠበቅና የማጽናት ግዴታ እንዳለባቸውና ኢትዮጵያን የሚገጥሟት ማናቸውም የውስጥ ችግሮች በውይይት፣ በሰላም እና በብሔራዊ መግባባት ሊፈቱ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በላሉ ኢታላ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: