የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ያደረጉት የሥራ ጉብኝት እና የሰጡት ቃል የመደመር መንግሥት ዘመናዊና ጽኑ ተቋማትን ለመገንባት ለያዘው ስትራቴጂካዊ ራዕይ ትልቅ ማሳያ ነው።
የተለዋዋጭ የአየር ንብረት ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም፣ ሳይንሳዊ መረጃዎችን የማመንጨት እና የመተንተን አቅምን ማሳደግ አማራጭ የሌለው ብሔራዊ ጉዳይ መሆኑን ያረጋገጠው ይህ ተቋም፣ ለኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋፅዖ በሀገር ደረጃ የተሰጠውን ልዩ ትኩረት ያሳያል።
የሳይንስና የቴክኖሎጂ አቅምን በማጎልበት የሕዝብን ደኅንነት እና ብሔራዊ ሀብትን የመጠበቅ ተልዕኮ፣ የመደመር ፍልስፍና ዋና ማዕከል በሆነው ተቋማዊ ራስን የመቻል እና የረጅም ጊዜ አቅም ግንባታ መርህ ላይ የተመሰረተ ነው።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ታሪካዊ ጉዞ ሲፈተሽ ከሰባት አስርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረ እና ደረጃ በደረጃ እያደገ የመጣ የረጅም ዘመን መሠረት ያለው ተቋም መሆኑን እንረዳለን።
በ1943 ዓ.ም በሲቪል አቪዬሽን መሥሪያ ቤት ሥር ለአቪዬሽን ደኅንነት አገልግሎት በትንሽ ክፍል ደረጃ የተጀመረው ይህ ሥራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ በመምጣቱ በ1973 ዓ.ም በዐዋጅ ብሔራዊ የሜትሮሎጂ አገልግሎቶች ኤጀንሲ ሆኖ በራስ ገዝነት እንዲደራጅ ተደርጓል።
በ1997 ዓ.ም ወደ ብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ በ2013 ዓ.ም ደግሞ አሁን ወደሚገኝበት የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ደረጃ ከፍ ማለቱ ተቋሙ ከቀላል የአየር ሁኔታ ምልከታ አልፎ ሁለገብ የሳይንስ እና የጥናት ማዕከል መሆኑን ያረጋግጣል።
ተቋሙ እያመጣ ያለው ጥልቅ የቴክኖሎጂ እና የአሠራር ለውጥ ከሳተላይት ምልከታ ባሻገር በመላው ኢትዮጵያ የተዘረጉ ጠንካራ የመረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎችን እና የመረጃ ማዕከላትን አቅም በማቀናጀት ላይ የተመሰረተ ነው።
አዲሱ የለውጥ ምዕራፍ ዘመናዊ አውቶማቲክ የአየር ንብረት ጣቢያዎችን፣ የራዳር ቴክኖሎጂዎችን እና የሳተላይት መረጃዎችን ከምድር ምልከታዎች ጋር በማቀናጀት ከፍተኛ ጥራት ያለው መረጃን እንዲያመርት አስችሎታል።
ይህ ዘመናዊነት ተቋሙ በዓለም አቀፉ የሜቲዎሮሎጂ ድርጅት በኩል ለአፍሪካ አህጉር የሥልጠና ማዕከል ሆኖ እንዲመረጥ ያደረገው ሲሆን፣ ይህም የኢትዮጵያን የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ልዕልና በአህጉራዊ ደረጃ ያደመቀ ታላቅ ስኬት ነው።
ሚቲዎሮሎጂያዊ መረጃዎች ወደ ተግባራዊ መመሪያ ሲቀየሩ ሕይወትን ይታደጋሉ፣ ሀብትን ይጠብቃሉ፣ እንዲሁም የተሻለ ውሳኔ ለመስጠት ያግዛሉ።
ዛሬ ላይ ተቋሙ የሚያመርታቸው የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎች ለግብርና፣ ለውኃ ሀብት፣ ለሕዝብ ጤና፣ ለአቪዬሽን እና ለአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ዘርፎች የጀርባ አጥንት ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።
በተለይም የዝናብ እና የሙቀት ሁኔታዎችን አስቀድሞ በመተንበይ በቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት አማካኝነት የትኞቹ አካባቢዎች ላይ ጣልቃ ገብነት ይበልጥ እንደሚያስፈልግ ለመወሰን የተካሄደው ሥራ የዜጎችን ሕይወት ከመታደግ ባሻገር የኢትዮጵያን የተፈጥሮ አደጋ የመቋቋም አቅም በከፍተኛ ደረጃ አጠናክሮታል።
በሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እና በመረጃ መሠረተ-ልማት ላይ የተደረገው ዘላቂ መዋዕለ-ንዋይ ተቋሙን ከቀደመው የድጋፍ ሰጪነት ሚና ወደ ብሔራዊ ልማትና ደኅንነት መሪነት አሸጋግሮታል።
ይህ ስኬት የመደመር መንግሥት ለተቋማት ግንባታ የሰጠውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው። በዚህም አስተማማኝ የመረጃ መሠረት ያለው እና ለተፈጥሮ ፈተናዎች ያልተንበረከከ ተቋም መገንባት ለወደፊቱ የኢትዮጵያ ብልጽግና ወሳኝ ምሰሶ መሆኑን በተግባር አረጋግጧል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: