በዓለም የታሪክ ድርሳናት ውስጥ የባሕር መውጫ በር ማጣት የሕዝቦችን የኢኮኖሚ ህልውና እና ብሔራዊ ሉዓላዊነት ለከፍተኛ አደጋ የሚያጋልጥ የታሪክ አጋጣሚ ነው።
ሆኖም በፅናት፣ በበሰለ ዲፕሎማሲ እና በሕዝባዊ ቁርጠኝነት የታጣን ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መብት መልሶ ማጎናጸፍ እንደሚቻል የፖላንድ ታሪክ ሁነኛ ማረጋገጫ ነው።
ዛሬ ኢትዮጵያ የባሕር በሯን ዳግም ለማግኘት የምታደርገው ጥረት፣ ፖላንድ ከባልቲክ ባሕር ጋር የተያያዘችበትን ታሪካዊ መስመር ከማስመለስ ሂደት ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል።
በፈረንጆች የጊዜ ቀመር በ18ኛው ክፍለ ዘመን ማጠቃለያ አካባቢ ማለትም እ.አ.አ በ1772፣ በ1793 እና በ1795 ፖላንድ በወደቀችበት ውስጣዊ የፖለቲካ ድክመት ምክንያት በወቅቱ ኃያላን በነበሩት ጎረቤቶቿ ኦስትሪያ፣ ሩሲያ እና ጀርመን ተከታታይ ወረራ ተፈጸመባት።
ምንም እንኳን እንደ ታዴኡሽ ኮስቲዩሽኮ ያሉ የነፃነት ታጋዮች ሕዝባዊ አመጽ ቢቀሰቅሱም፣ እነዚህ ጎረቤት ኃይሎች ፖላንድን ሙሉ በሙሉ በመከፋፈል ከዓለም ካርታ አጠፏት።
ይህ ክስተት የታሪክ ድርሳናት "የፖላንድ መከፋፈል" በሚል የሚጠሩት ሲሆን፣ በሂደቱም ፖላንድ ከመካከለኛው አውሮፓ የባሕር በር ከሆነው የባልቲክ ባሕር ሙሉ በሙሉ ተነጠለች።
ፖላንዳውያን ለ123 ዓመታት ያህል የነፃነት እና የሉዓላዊነት ጥያቄያቸውን ሳያቋርጡ ብርቱ ትግል አድርገዋል።
የረጅም ዘመን የዜጎች ተጋድሎ፣ የዓለም አቀፍ ፖለቲካዊ ለውጦች እና በሳል ዲፕሎማሲ ተሰናስለው አንደኛው የዓለም ጦርነት እ.አ.አ በ1918 ሲጠናቀቅ ፖላንድ እንደ አዲስ ዳግም ተወለደች።
እ.አ.አ በ1919 በተፈረመው የቨርሳይል ውል (Treaty of Versailles) አንቀጽ 87 መሰረት "የፖላንድ ኮሪደር" (Polish Corridor) በመባል የሚታወቀው የመሬት መስመር ከጀርመን ተቆርጦ ለፖላንድ እንዲሰጥ ተደረገ። ይህም መስመር ፖላንድን ከባልቲክ ባሕር ጋር ዳግም ያገናኛት ወሳኝ የባሕር መውጫ ሆነ።
ፖላንድ የባልቲክ ባሕር በሯን ካገኘች በኋላ በራሷ ጥረት "ግዲኒያ" (Gdynia) የተሰኘችውን ታላቅ የወደብ ከተማ ከባዶ በመገንባት፣ ጀርመንን፣ ሩሲያን እና የስካንዲኔቪያን ሀገራትን የሚያገናኝ የቀጣናው ታላቅ የንግድ ማዕከል አደረገቻት።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከፍተኛ ውድመት ቢደርስባትም፣ የባሕር በሯን መሠረት በማድረግ ባሳየችው የኢኮኖሚ ትንሣኤ ዛሬ የፖላንድ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) ከ1 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ በማሻገር በአውሮፓ ኅብረት ውስጥ ካሉ ጠንካራ ኢኮኖሚዎች አንዷ ለመሆን ችላለች።
የኢኮኖሚ ዕድገቷም ከአውሮፓ ኅብረት አማካይ በላይ እንዲሆን ያስቻላት ያኔ ያስከበረችው የባሕር በሯ መሆኑ አከራካሪ አይደለም።
ኢትዮጵያ የቅኝ ግዛት ሽንፈት ታሪክ ባይኖራትም፣ እ.አ.አ በ1993 በታሪክ አጋጣሚ እና በጂኦፖለቲካዊ ጫና ያጣችውን የባሕር በር ለማስመለስ የምታደርገው ጥረት እንደ ፖላንድ ያሉ ታሪካዊ ሂደቶችን እንደ ዋቢ የምታነሳበት አግባብ አላት።
በአሁኑ ወቅት በፍጥነት እያደገ ለመጣው እና ከ130 ሚሊዮን በላይ ለሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲሁም ለሰፊው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በአንድ ኪራይ ወደብ ላይ ብቻ ጥገኛ መሆንና በየዓመቱ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለወደብ አገልግሎት ማውጣት ከፍተኛ የኢኮኖሚና የደኅንነት ጫና ፈጥሯል።
የባሕር በር ማግኘት በዓለም አቀፍ ሕግጋት፣ በታሪክ፣ በተፈጥሯዊ መብት እና በዲፕሎማሲያዊ አማራጮች የሚረጋገጥ የህልውና ፍላጎት ነው።
ኢትዮጵያ የምትፈልገው የባሕር በሯን በማስመለስ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ በማደግ፣ የትራንስፖርት ወጪን እና ጊዜን በመቀነስ የቀጣናውን የኢኮኖሚ ትስስር ማጠናከር ነው።
ለዘመናት በዜጎች ልቦና ውስጥ የቆየውን ቁጭት የሚመልሰው የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ፣ ብሔራዊ ክብርን ከመመለስ ባሻገር የአፍሪካ ቀንድን የጋራ እድገትና ሰላም የሚያረጋግጥ ነው።
ስለሆነም ፖላንድ የባሕር መውጫዋን ለማስመለስ እንዳደረገችው ጥረት ሁሉ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ህልውና እና ታሪካዊ መብት ለማስከበር በበሰለ ዲፕሎማሲ እና በሰላማዊ መንገድ ወደ ቀይ ባሕር ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ዙሪያ መትጋት የእያንዳንዱ ዜጋ የማይተካ ድርሻ ነው።
#የመደመርመንግሥት #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በሜሮን ንብረት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: