Search

የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከፍታ፡- ብሔራዊ ጥቅምን ማረጋገጥ እና የኢኮኖሚ ብልፅግናን የመገንባት ጉዞ

ረቡዕ ጥቅምት 04, 2019 70

በፍጥነት በሚቀያየረው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ውስጥ የአንድ ሀገር ሕልውና፣ ዕድገትና ዘላቂ ደኅንነት የሚወሰነው በውስጣዊ ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን ከውጭው ዓለም ጋር በሚደረግ ስልታዊና ውጤታማ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ነው።

የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ የሀገርን ሉዓላዊነት እና ነፃነት ያለ ጦርነትና ግጭት ለማስጠበቅ የመጀመሪያው የደኅንነት መስመር በመሆን ከግጭት ይልቅ ውይይትን፣ ከመገለል ይልቅ ትብብርን እንዲሁም ዓለምን በወዳጅና ጠላት ከማቀፋፈል ይልቅ በጋራ ጥቅም ማስተሳሰርን መርህ አድርጎ አዲስ የውጭ ግንኙነት ምዕራፍ ከፍቷል።

ኢትዮጵያ በመደመር መንግሥት መሪነት ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር፣ የሰላም ግንባታን ለማረጋገጥና የልማት ግቦቿን ለማሳካት የሚያስችላትን የነቃና ሰፊ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ትገኛለች።

የሀገር ግንባታ ያለ ጠንካራና ዘላቂ ኢኮኖሚ ሊታሰብ የማይችል በመሆኑ፣ ውጤታማ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ በመከተል ረገድ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ አዳዲስ የገበያ አማራጮችን በመክፈትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማመቻቸት አበረታች ሥራዎች ተከናውነዋል።

ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትና የልማት አጋሮች ጋር በተመሰረተው ግንኙነት የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን ለማስፋፋት፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል እንዲሁም የዲያስፖራውን ማኅበረሰብ ዕውቀት፣ ልምድ እና ሀብት በማስተባበር በሀገር ግንባታ ሂደት ንቁ ተሳታፊ በማድረግ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የነበራትን የንግድ፣ የመሰረተ ልማት እና የቀጣናዊ ሰላም ትስስር ከማጠናከር ባሻገር በእስያና በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲዋን በስፋት እያንቀሳቀሰች ትገኛለች።

በተጨማሪም የዓባይ ወንዝን ጨምሮ የውኃ ሀብቷን በፍትሃዊና ምክንያታዊ መርህ የመጠቀም ሕጋዊ መብቷን ማስከበሯ፣ እንደ አረንጓዴ ዐሻራ ያሉ ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃ ተነሳሽነቶችን መተግበሯ እንዲሁም በአፍሪካ ሕብረትና በሌሎች ባለብዙ ወገን መድረኮች ያላትን ተሳትፎ ማሳደጓ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተደማጭነት እና ተሰሚነት ወደ ተጨባጭ ደረጃ ያሸጋገረ ስኬት ሆኗል።

የዚሁ አዲስ የዲፕሎማሲ ከፍታና ተስፋ ሰጪ ስኬት ጉልህ ማሳያ የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት ነው። ኢትዮጵያን ጨምሮ 11 ሙሉ አባላት እና 10 አጋር ሀገራት የታቀፈውን ይህን ግዙፍ ትብብር ማዕቀፍ መቀላቀሏ በዓለም አቀፍ አጀንዳዎች ላይ ድምጿን ለማሰማትና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ሳቢነቷን ለማሳደግ ትልቅ ዕድል ፈጥሮላታል።

በቅርቡ በህንድ ኒው ዴልሂ በተካሄደው 18ኛው የብሪክስ መሪዎች ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በስብስቡ ውስጥ ያሉትን ካፒታል፣ ቴክኖሎጂና ገበያ ከኢትዮጵያ የማዕድን፣ የታዳሽ ኃይል፣ የግብርናና የኢንዱስትሪ አቅም ጋር በማስተሳሰር የጋራ ዕሴት ለመፍጠር ሀገራችን ዝግጁ ናት።

ሀገራችን በዘረጋችው ጠንካራ ዲፕሎማሲ አማካኝነት የሀገርን ባህል፣ ታሪክ፣ ዕሴቶችና አዎንታዊ ገጽታ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማስተዋወቅ ተችሏል። ይህም የቱሪዝም ዘርፍን ከመደገፍ ባሻገር ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ውሳኔዎች እና መድረኮች ላይ ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነት አጎልብቷል።

በመሆኑም ብሔራዊ ጥቅም፣ ዘላቂ ሰላምና የጋራ ዕድገትን ማዕከል ያደረገው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ሀገራችንን ከተመልካችነት ወደ ተዋናይነት፣ ከተጠቃሚነት ወደ አምራችነት እንዲሁም ከተሳታፊነት ወደ ዓለም አቀፍ አጀንዳ ቀራጭነት ሚና በማሸጋገር ላይ ይገኛል።

በብሌን ደምበሎ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: