በፍጥነት እየተለወጠ በሚገኘው የዓለም አቀፍ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሥርዓት ውስጥ የሀገራትን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ፣ የቀጣናውን ሰላም ማረጋገጥ እና ዘላቂ ልማትን ማፋጠን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ዋነኛ ዓላማዎች ናቸው።
ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካና በአጠቃላይ አፍሪካ አህጉር ያላትን ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊ እና የጂኦ-ስትራቴጂያዊ የበላይነት መሠረት በማድረግ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋን በወቅታዊው የዓለም ሁኔታ ልክ ማስተካከል ግድ ብሏታል።
በመደመር እሴቶች ላይ የተገነባው የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የቀደሙ መልካም ተሞክሮዎችን በማስቀጠል፣ ጉድለቶችን በማረም እና የነገውን ዕድል ታሳቢ በማድረግ የተቃኘ ነው። ይህ ስትራቴጂ ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል ያደረገ፣ ሚዛናዊና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ እንዲሁም ከተግባር ተኮር አካሄድ ጋር የተጣመረ ነው።
የሀገር ሉዓላዊነት፣ የሕዝቦች ደኅንነትና የኢኮኖሚ እድገት የየትኛውም ዲፕሎማሲያዊ ድርድርና ግንኙነት መሠረታዊ መለኪያዎች ናቸው። ኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነቷ የምትከተለው አቋም በአንድ ወገን ጥገኝነት ላይ የተመሠረተ ሳይሆን፣ ሁለንተናዊና ሚዛናዊ የዲፕሎማሲ መስመርን የተከተለ ነው። ይህም በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የሀገርን ድምፅና የመደራደር አቅም ከፍ አድርጎታል።
ሀገራችን በማንኛውም የውጭ ተጽዕኖ እና ጣልቃ ገብነት ሥር ሳትወድቅ ብሔራዊ ጥቅሟን በራሷ ውሳኔ የማስከበር መብቷን በማረጋገጥ፣ የሀገርን ክብር ያስጠበቀ ዲፕሎማሲ በመተግበር ላይ ትገኛለች።
የመደመር ዲፕሎማሲ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን አሳልፎ ሳይሰጥ፣ ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ጋር በመከባበርና በእኩልነት መርህ ላይ በተመሠረተ መንገድ የመገናኘት ስትራቴጂ ነው።
በዘመናዊው የዲፕሎማሲ አካሄድ የፖለቲካ ግንኙነት ብቻውን በቂ ባለመሆኑ፣ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የመደመር መንግሥት የውጭ ፖሊሲ ዋነኛ ክንፍ ሆኗል።ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ፣ የወጪ ንግድን ለማሳደግና አዳዲስ የገበያ ዕድሎችን ለመክፈት ሰፊ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ እያደረገች ትገኛለች። የተጀመሩት የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችና የፋይናንስ ዘርፉን ክፍት የማድረግ አሰራር ለውጭ ኢንቨስተሮች ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል።
ከበለጸጉ ሀገራትና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በሚደረጉ ስምምነቶች የዲጂታል ኢኮኖሚ፣ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ የታዳሽ ኃይል እና የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ስትራቴጂያዊ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታና የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር የዚህ ስትራቴጂ ግልጽ ማሳያዎች ሲሆኑ፣ ታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይሏን ለሱዳን፣ ለጂቡቲ እና ለኬንያ በማቅረብ ላይ ትገኛለች።
ኢትዮጵያ የፓን-አፍሪካኒዝም መንፈስ መጋቢና የነጻነት ምልክት በመሆኗ፣ ለአፍሪካ አህጉር አንድነትና እድገት የምታደርገው ጥረት በመደመር ፖሊሲ ውስጥ ልዩ ቦታ ተሰጥቶታል።
አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን በመደገፍና በመተግበር፣ አፍሪካውያን በራሳቸው ሀብትና ገበያ እንዲጠቀሙ ንቁ ተሳትፎ እያደረገች ነው።
ኢትዮጵያ የብሪክስ ስብስብ አባል መሆኗ የዲፕሎማሲያዊና የኢኮኖሚ አቅሟን ያሳደገ ታላቅ ታሪካዊ ክስተት ነው። ይህም የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲዋን በማስፋት፣ ከደቡብ-ደቡብ ትብብር ከፍተኛ ጥቅም እንድታገኝ ያስችላታል።
የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ከባህላዊና ከቀደሙት የፖለቲካ ወገንተኝነቶች በማውጣት፣ ብሔራዊ ጥቅምን፣ የጋራ ተጠቃሚነትንና ተግባር ተኮር ስትራቴጂን መሠረት ያደረገ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።
ኢትዮጵያ ይህንን ሚዛናዊና ዘመናዊ የዲፕሎማሲ መስመር አጠናክራ በመቀጠል፣ የራሷን የልማትና የሰላም ፍላጎት ከቀጣናውና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር አስተስስራ ዘላቂ ውጤት ማምጣቷን ታረጋግጣለች።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: