ህወሓት ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ዋና ፍላጎቱ እና አጀንዳው የሕዝብን ጥያቄ መመለስ ሳይሆን የግል እና የቡድን ሥልጣንና ጥቅምን ማሟላት ነው ሲሉ የቀድሞው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ ገለጹ።
አቶ አባዱላ በወቅታዊ የሀገራችን የፖለቲካ እና የልማት ሁኔታዎች ላይ በሰጡት አስተያየት፣ የትግራይ ሕዝብ ላለፉት 50 ዓመታት ልጆቹን ለጦርነት ገብሮ በድህነት ውስጥ ሲኖር የቆየ መሆኑን ጠቅሰው፣ የድርጅቱ ፍላጎት የሕዝብ ቢሆን ኖሮ ሕዝቡን ወደ ሌላ እልቂት ከመክተት ይልቅ ለሰላም ይቆም እንደነበር ተናግረዋል።
ህወሓት ከሥልጣን ማማ ሲወርድ ሀገር ለማፍረስ እና ሰላም ለማደፍረስ ሲሠራ መቆየቱንም ጠቁመዋል።
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ትልቅ የሰላም ዕድል ይዞ መምጣቱን እና በአሁኑ ወቅት በአንድነት የተነሣውን ትልቅ መንግሥት እና ሀገር ማፍረስ እንደማይቻል አስረድተዋል።
በሌላ በኩል የቀይ ባሕርን እና የዓባይን ጉዳይ በመጠቀም ኢትዮጵያ እንዳታንሰራራ የሚሠሩ የውጭና የውስጥ ኃይሎች ሴራ ከንቱ መቅረቱን የጠቆሙት አቶ አባዱላ፣ ለዚህም ማረጋገጫው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያለምንም የውጭ ብድር እና ድጋፍ በኢትዮጵያውያን አቅም የተገነባ መሆኑ ነው ብለዋል።
አሁን ያለችው ኢትዮጵያ በሌላ ደረጃ ላይ የምትገኝ በመሆኗ፣ ከሀገራችን ጋር በሰላማዊ መንገድ እና በ"ሰጥቶ መቀበል" ፖሊሲ ብቻ አብሮ ከመሥራት ውጭ ሌሎች አማራጮች የተዘጉ መሆናቸውን አፅንኦት ሰጥተዋል።
የትግራይን ጉዳይ ወደ ሰላም ለማምጣት ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር እየሠሩ ያሉ የቀድሞ እና የአሁኑ የትግራይ ፖለቲከኞችን ያደነቁ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ሁልጊዜም ቢሆን ለይቅርታ ክፍት መሆኑን በማስገንዘብ ሌሎችም ይህንን የሰላም መንገድ እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል።
#የመደመርመንግሥት #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: