በዓለም አቀፍ መድረኮች የሀገርን ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር፣ የዜጎችንም ክብርና መብት ለመጠበቅ በፅናትና በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት ውድ ዋጋ ለሚከፍሉ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች እውቅና የሚሰጥበት “የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ቀን” በዛሬው ዕለት በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።
ዕለቱ ለዲፕሎማቶቻችን የሚገባውን እውቅና ከመስጠት ባሻገር፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍና በቀጣናዊ መድረኮች ያላትን ሚና ይበልጥ ለማጠናከር እና ብሔራዊ ጥቅሟን በጽኑ አቋም ለማስጠበቅ የሚደረግ ጥረት ነው።
ዲፕሎማሲ አመቺ ሁኔታዎች ባሉባቸው አካባቢዎች ብቻ የሚከናወን ሳይሆን፣ ይልቁንም ግጭት፣ አለመረጋጋት እንዲሁም የተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በስፋት በሚታዩባቸው አዳጋች ቀጣናዎችና የዓለም ክፍሎች ጭምር የሚፈጸም፣ ከፍተኛ መስዋዕትነትን እና የሀገር ፍቅርን የሚጠይቅ የፊት መስመር ተጋድሎ ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ለኢቢሲ ዶትስትሪም እንደገለጹት፣ ዲፕሎማቶቻችን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ክብር በዓለም አቀፍ መድረክ ለማስጠበቅ፣ በፅናትና በከፍተኛ የሀገር ወዳድነት ስሜት ሌት ተቀን በትጋት በመሥራት ላይ ይገኛሉ።
ዛሬ እየተከበረ ያለው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ቀን፣ የሀገራችንን ዓለም አቀፋዊ ተሳትፎ ለማጎልበት ለሚጥሩ የዘርፉ ባለሙያዎች ተገቢውን ዕውቅና ከመስጠቱም በላይ፣ የኢትዮጵያን ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ያለንን ጽኑ አቋም የምናድስበት ታሪካዊ መድረክ ነው በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ መድረክ ረጅም፣ ኩሩና ታሪካዊ መሠረት ያላት ሀገር ናት። በቅርብ ጊዜያት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያዘጋጀውን የዲፕሎማሲ ሳምንትና ኤግዚቢሽን ጨምሮ የተከናወኑ የለውጥ ሥራዎች እንደሚያሳዩት፣ የሀገራችን ዲፕሎማሲያዊ ጉዞ ከጥንታዊ የንግድና የወዳጅነት ግንኙነቶች ተነስተው እስከ ዘመናዊው የዲፕሎማሲ አሠራር የዘለቁ በርካታ ስኬቶችን ያካተተ ነው።
በወቅታዊው የዓለም አቀፍ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ውጥረት ውስጥ፣ የሀገርን ጥቅም ሳያስደፍሩና ብሔራዊ ክብርን አስጠብቆ መጓዝ የዲፕሎማቶች ጥራትና የዘመነ ዕውቀት ይጠይቃል።
ይህ ዕለት የዲፕሎማቶቻችንን መስዋዕትነት እያሰቡ ማመስገን ብቻ ሳይሆን፣ የነገዋን ጠንካራና ተፅዕኖ ፈጣሪ ኢትዮጵያን ለመገንባት በዲፕሎማሲው ዘርፍ የሰው ኃይል ልማትንና ዘመናዊ አሠራሮችን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ የሚያስገነዝብ ነው።
#የመደመርመንግሥት #ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ
በላሉ ኢታላ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: