ኢትዮጵያ በታሪኳና በጂኦፖለቲካዊ አቀማመጧ የአፍሪካ የኩራት ምንጭ ናት። ዛሬ ላይ ሆነን ስንመለከት፣ የሀገራችን የአቪዬሽን ዘርፍ ጉዞ ከትራንስፖርት አገልግሎት ባለፈ የብሔራዊ ኩራት እና የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን አንዱ የጀርባ አጥንት ሆኗል።
በዚህም መሠረት በቢሾፍቱ አካባቢ እየተገነባ የሚገኘው ታላቁ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት የ #ትልቅ_ሀገር፣ #ትልቅ_ሕዝብ እና የ#ታላቅ_ርዕይ ሕያው መገለጫ ነው።
የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታው በመደመር መንግሥት የተጀመረ የሕዝባችንን የመሥራት አቅም፣ የመሪዎቻችንን የሩቅ ራዕይ እና የትውልድን የወደፊት ተስፋ የሚያሳይ ታሪካዊ ፕሮጀክት ነው።
አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ባለፉት ዓመታት ያከናወነው አመርቂ ሥራና ያሳየው ፈጣን ዕድገት የአፍሪካ አቪዬሽን መሥመር እንዲሆን አስችሎታል።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እያሳየ ያለው እጅግ ፈጣን ለውጥ እና የተጓዦች ዕድገት አሁን ያለውን አቅም እንዲያሳድግ አስገድዶታል።
ይህ ፕሮጀክት ኢትዮጵያውያን ተነስተን ስንሠራ የማይቻል ነገር እንደሌለ የሚያረጋግጥ፣ የብሔራዊ ኩራታችን ማማም ጭምር ነው።ቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያን በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በግንባር ቀደምትነት የሚያስቀምጥ ግዙፍ ማዕከል ይሆናል።
አፍሪካን ከቀሪው ዓለም ጋር የሚያገናኝ ዋና መተላለፊያ በመሆን የዓለም አቀፍ አቪዬሽን ማዕከልነታችንን የሚያጠናክር እንዲሁም ሀገራችን ወደ ላቀ የኢንዱስትሪ፣ የአገልግሎት እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም የምታደርገውን ሽግግር በእጅጉ ያፋጥናል።
የዚህ ግዙፍ ፕሮጀክት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳዎች ዘርፈ ብዙ እና የረጅም ጊዜ መሠረት ያላቸው ሲሆኑ፣ ሀገራችን ያሏትን ታሪካዊ እና የተፈጥሯዊ ሀብቶች ለዓለም ተደራሽ በማድረግ የቱሪስቶች ፍሰት እንዲጨምር ያደርጋል።በግንባታው ሂደትም ሆነ ሲጠናቀቅ በአቪዬሽን፣ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በንግድ እና በሌሎች አገልግሎት ሰጪ ዘርፎች ለአጭርና ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ እጅግ በርካታ የሥራ ዕድሎችን ይፈጥራል።
ከአዲስ አበባ በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እየተገነባ የሚገኘው አዲሱ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ በዓመት እስከ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል። ይህም የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አሁን ያለውን የማስተናገድ አቅም በ4.4 እጥፍ የሚያሳድግ ግዙፍ ፕሮጀክት ያደርገዋል።
ይህ ታሪካዊ ፕሮጀክት፣ ሀገራችንን ከዓለም ቀዳሚ የአቪዬሽን ማዕከላት ተርታ ለማሰለፍ፣ በደረሰበት ሁሉ ሰንደቅ ዓላማችንን ከፍ አድርጎ የሚያሳይ እና የአኅጉራችን ኩራት በሆነው በኢትዮጵያ አየር መንገድ አማካኝነት በአፍሪካና ከዚያም ባሻገር ያለውን ትስስር ለማጠናከር ሌሊትና ቀን በከፍተኛ ጥረት እየተገነባ ይገኛል።
የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተደራሽነት ከማሳደግ ባለፈ በአፍሪካ እና በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ያላትን ሚና ከፍተኛ ደረጃ የሚያደርስ ነው።ፕሮጀክቱ የጠንካራ አመራር፣ የሕዝብ አብሮነት እና የላቀ ራዕይ ውጤት ነው። #ትልቅ_ሀገር፣ #ትልቅ_ሕዝብ፣ እና #ታላቅ_ርዕይ በሚሉ አቅጣጫዎች የሚመራው ይህ የልማት ምዕራፍ፤ የኢትዮጵያን የነገ ብልጽግና በሰማይና በምድር አጽንቶ የሚያኖር የታሪክ ዐሻራ ነው።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: