የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካለኝ (ዶ/ር) በዓለም አቀፉ የመንግሥታት የብድር ክብ ጠረጴዛ መድረክ ላይ በመገኘት የኢትዮጵያን የብድር ሽግሽግ ተሞክሮ እና ዋና ዋና ትምህርቶች አቅርበዋል።
ባንክ ገዥው ተሞክሮውን ያቀረቡት በባንኮክ ታይላንድ በተካሄደው የ2026 የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን በተካሄደ መድረክ ላይ ነው።
ዶክተር ኢዮብ በንግግራቸው፣ ለአዲስ አመልካች ሀገራት የብድር ሽግሽግ ሂደቱ የተቀላጠፈ እና ግልጽ የጊዜ ሰሌዳን የተከተለ ሊሆን እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
አክለውም በአበዳሪዎች መካከል የተሻለ ቅንጅት እንዲኖር እና ለአማካሪዎች የሚከፈለው ክፍያ ገደብ እንዲበጅለት ጥሪ አቅርበዋል። ወደፊት በሚከናወኑ ተግባራት ላይ የዓለም አቀፍ የመንግሥታት ዕዳ ውይይት መድረክ (GSDR) የሥራ ፕሮግራም በብሪተን ውድስ ተቋማት (IMF እና ዓለም ባንክ) መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር እንዳለበት የኢትዮጵያ ምክረ ሐሳብ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የብድር ሽግሽግ ካደረጉ በኋላ በጊዜያዊነት የብድር ደረጃቸው (Credit Rating) ዝቅ ላሉ ሀገራት የተቀመጡ ጠንካራ የመስፈርት ገደቦችን እንደገና መገምገም እና የልማት አጀንዳዎችን የሚደግፉ አዳዲስ የፋይናንስ አቅርቦቶችን በቅንጅት ማመቻቸት ላይ ትኩረት ተደርጎ መሠራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: