Search

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን የዳንጎቴ ነዳጅ ኩባንያን የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ሽያጭ አስጀመረ

ሓሙስ ጥቅምት 05, 2019 63

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን የናይጄሪያው ግዙፍ ኩባንያ የዳንጎቴ ፔትሮሊየም እና ነዳጅ ማጣሪያ ኩባንያ የመጀመሪያ ደረጃ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ  ሕዝባዊ ሽያጭ ማስጀመሪያ ፕሮግራሙን አካሂዷል።

ዳንጎቴ ፔትሮሊየም ሪፋይነሪ፣ በኢትዮጵያ ለሚያደርገው የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ግብይት ከጠቅላላ ሀብቱ 10 በመቶ የሚሆነውን ለገበያ ያቀረበ ሲሆን፣ ይህም በቁጥር 4.1 ቢሊዮን የአክሲዮን ሽያጮችን የሚያካትት ነው።

የኢንቨስትመንት መስፈርቶችን ለሚያሟሉ ብቁ ባለሀብቶች አንድ አክሲዮን የመግዣ ዋጋ 74 ነጥብ 9 ብር ተመን ወጥቶለታል።

አክሲዮኖቹን ለሕዝብና ለባለሀብቶች የማሻሻጥና የመሸጥ ሂደት በሕጋዊ መንገድ ፈቃድ በተሰጣቸው 3 አገበያይ አገናኝ ኩባንያዎች በኩል የሚከናወን ይሆናል።

እንደ ዳንጎቴ ያለ አህጉራዊ ግዙፍ ኩባንያ የሀገሪቱን የካፒታል ገበያ መቀላቀሉ በኢትዮጵያና በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድና የኢኮኖሚ ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል ተብሎ ይታመናል።

ከዚህ በተጨማሪም የውጭ ሰነዶችን በሀገር ውስጥ ማሻሻጥ የሚያስችል ሕጋዊ አሠራር መፈጠሩ፣ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች በቀጣይነት በዓለም አቀፍ ደረጃ በትልልቅ የውጭ ኢንቨስትመንቶች ላይ በቀጥታ ተሳታፊ እንዲሆኑና የሀብት አማራጮቻቸውን እንዲያሰፉ ሰፊ ዕድል የሚፈጥር ነው።                     

ግዙፉ የዳንጎቴ ግሩኘ እአአ በ2030 አጠቃላይ ዓመታዊ ገቢውን 100 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ አቅዶ እየሠራ መሆኑን አሳውቆ፤ በኢትዮጵያ የተጀመረው የድርሻ ሽያጭ ሀገሪቱን ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ነው ብሏል። 

በመቅደስ እንዳለ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: