የህዋ ምርምር እና የቴክኖሎጂ ኩባንያው ስፔስ ኤክስ (SpaceX) ከኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አምራቹ ቴስላ (Tesla) ጋር በመሆን፣ በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ታሪክ ውስጥ በአይነቱ ልዩ የሆነውን “ቴስላ ሮድስተር” የተሰኘ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ በ2028 ለማምረት ማቀዳቸውን ይፋ አደረጉ።
ባለው ቅንጡ አሰራር እና ዘመኑን ባወጀ የቴክኖሎጂ ጥበብ ትልቅ መነጋገሪያ የሆነው ይህ አዲስ ሞዴል ይፋ በተደረገበት ወቅት፤ ከአካላዊ መሰናክሎች በቀላሉ የመዝለል እና በአየር ላይ የመሽከርከር አቅም ያለው በመሆኑ በዘርፉ ባለሙያዎች ዘንድ ከፍተኛ አግራሞትን ጭሯል።
ይህ ተሽከርካሪ አካላዊ ፈተናዎችን በቅልጥፍና ከመሻገር ባለፈ በአንድ ሰከንድ ውስጥ ብቻ ከዜሮ ፍጥነት ተነስተው ወደ 80 ማይል በሰዓት የመወንጨፍ አስደናቂ አቅም እንዳለው ተገልጿል።
የኩባንያው ባለቤት ኤሎን መስክ ዓላማ ደግሞ የተሽከርካሪውን ፍጥነት ከድምፅ ፍጥነት በግማሽ ያነሰ ማለትም በሰዓት 616 ኪሎ ሜትር ያህል ማድረስ ነው።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2017 ይፋ ተደርጎ በ2020 ወደ ገበያ ይወጣል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው ይህ ተሽከርካሪ፤ በ2027 እና በ2028 ለገበያ ሲቀርብ በጣም ውስን ለሆኑ ግለሰቦች እጅግ ውድ በሆነ ዋጋ እንደሚሸጥ ታውቋል።.
የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ተንታኞች እንደሚሉት ይህ እርምጃ ቴስላ ለሰፊው ገበያ ከዚህ በፊት ላቀረባቸው መደበኛ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ገበያ የመፍጠር አዲስ ዘዴ ነው።
በሌላ በኩል ባለፉት ሁለት ዓመታት የቴስላ ተሽከርካሪዎች ሽያጭ መቀነሱን የጠቆሙት የዘርፉ ኢንቨስተሮች፤ ይህ ቅንጡ ተሽከርካሪ ከዘመናዊነቱ በዘለለ ለቴስላ ኩባንያ ገቢ ያን ያህል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላይኖረው እንደሚችል ገልጸዋል።
በመሆኑም ኩባንያው ከእንደዚህ አይነት የቅንጦት ተሽከርካሪዎች ይልቅ ለሰፊው ገበያ እና ለማህበረሰቡ በቀላሉ ሊቀርቡ በሚችሉ ተሽከርካሪዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: