የኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ሲታወስ በአብዛኛው በሃይል አሰላለፍ፣ በግጭት እና ልዩነቶችን በጦር መሳሪያ የመፍታት ሰፊ ተጽዕኖ ውስጥ አልፎ መምጣቱ ይታወሳል።
የሃሳብ ልዩነትን በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት ፈንታ በጉልበት ለመፍታት መሞከር፣ ለዓመታት የሀገራችንን ሰላም፣ ዕድገት እና የሕዝብ ደህንነት ሲፈትን ቆይቷል።
ይሁን እንጂ ዛሬ ኢትዮጵያ ይህንን አጥፊ የፖለቲካ ሰንሰለት ሰብራ፣ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ የሚያስተናግድ እና ሕዝባዊ ውሳኔን ማዕከል ያደረገ አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት ታሪካዊ ሽግግር ላይ ትገኛለች።
ይህ ከጠመንጃ ባህል ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ልምምድ የሚደረግ ሽግግር ቀላል እና በአንድ ቀን የሚሳካ አይደለም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዲሞክራሲያዊ ውድድር ውስጥ የፓርቲዎች ማሸነፍና መሸነፍ ቢኖርም ኢትዮጵያ ግን አሸናፊ እንጂ ተሸናፊ ልጆች የሉዋትም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አሸናፊነትን በጉልበት ከማስፈን ይልቅ፣ በሃሳብ የበላይነት ማሸነፍ፣ መቻቻልን ማዳበር እና ሕጋዊ ውድድርን መቀበልን ይጠይቃል።
የመደመር መንግሥት «ልዩነቶችን በውይይት፣ ዴሞክራሲያዊ ሂደቶችን ደግሞ በሰላማዊ ፉክክር እንፍታ» በሚል ጽኑ አቋም እያከናወናቸው ያሉ የፖለቲካና የሕግ ማሻሻያዎች፣ የዚህ ታሪካዊ ሽግግር ማዕበል ዋና አንቀሳቃሾች ናቸው።
ፖለቲካን የደም መፋሰሻ ሳይሆን የልማት እና የዕድገት ውድድር ማድረጉ ለነገዋ ሀገር ህልውና ወሳኝ ነው።
በዚህ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ የሽግግር ጉዞ ውስጥ ሀገራዊ ምክክር የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ምህዳር ከመሠረቱ ለመገንባት የተወሰደ ታሪካዊ እና የላቀ እርምጃ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከተለያዩ ማህበራዊ ክፍሎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የህብረተሰብ ዕውቅና ያላቸው አካላት ጋር በመነጋገር፤ የዘመናት ቁስሎችን መታከም፣ በታሪካዊ አለመግባባቶች ላይ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ እና የሀገርን በጋራ መቅረጽ የዚህ ሂደት ዋና ዓላማ ነው።
ሀገራዊ ምክክሩ ያለፉትን አሻጥሮች እና የጠመንጃ ፖለቲካ ባህል በማስወገድ፣ ልዩነቶቻችንን በውይይት ጠረጴዛ ላይ ፈትተን በአብሮነት እንድንቀጥል ድልድይ እየዘረጋ ይገኛል።
ሰላማዊ የፖለቲካ ልምምድ እውን የሚሆነው የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራን፣ ሲቪክ ማህበራት እና መላው ዜጎች ሃላፊነትን በወሰደ መልኩ ሲንቀሳቀሱ ነው።
ኃይልን እንደ መፍትሔ የመቁጠር ያረጀ አስተሳሰብን በአግባብ በመታገል፣ ሕግን ማክበር እና የዴሞክራሲ ተቋማትን ማጠናከር ይገባል።
ዴሞክራሲያዊ ምርጫዎች፣ ነጻ ሃሳብን በሰለጠነ መንገድ ማራመድ እና ገንቢ ትችቶች የፖለቲካ መገለጫዎቻችን ሲሆኑ ብቻ ነው የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚቻለው።
በመሆኑም አዲሲቷን እና የበለጸገችዋን ኢትዮጵያ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት፣ ከጠመንጃ ፖለቲካ ሙሉ በሙሉ ተላቆ ወደ ሰላማዊ፣ ሀገራዊ ምክክርን ያማከለ እና ሕጋዊ ፉክክር መግባት የሁላችንም የጋራ ግዴታ ነው።
የዛሬው ትውልድ ያለፉትን መራራ ግጭቶች እንደ ትምህርት በመውሰድ፣ የሰላም፣ የውይይት እና የጋራ መግባባት ባህልን በፅኑ ሊያሰርጽ ይገባል።
ሰላም ሲረጋገጥ ልማት ይቀጥላል፤ የሰለጠነ ፖለቲካ ሲሰፍንም የሀገር ክብርና ሉዓላዊነት በዘላቂነት ይረጋገጣል።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: