Search

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ በ2025/2026 በጀት ዓመት 6.14 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ አገኘ

ቅዳሜ ጥቅምት 07, 2019 46

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ በ2025/2026 በጀት ዓመት 6.14 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን እና ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ293.6 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ገለጸ። የባንኩ ከግብር በፊት የተገኘ ትርፍ 11.47 ቢሊዮን ብር ደርሷል።

ባንኩ በ2025/2026 በጀት ዓመቱ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘቡን 193.26 ቢሊዮን ብር ያደረሰ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ10.3 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አብነት ታረቀኝ ገልጸዋል። አጠቃላይ የሀብት መጠኑም 224 ቢሊዮን ብር መድረሱን ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ በበጀት ዓመቱ 33.14 ቢሊዮን ብር ገቢ የሰበሰበ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ65.6 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው።

ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለችውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በመቀላቀል ባንኩ የዲጂታል ክፍያ አማራጮችን አስፋፍቷል። በዚህም ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ ከ67 ሺህ ለሚልቁ አርሶ አደሮች የዲጂታል ብድር መስጠት መቻሉን ምክትል የቦርድ ሰብሳቢው አብራርተዋል።

ባንኩ 42.73 ቢሊዮን ብር አዲስ ብድር ለአዳዲስ ፕሮጀክቶች የሰጠ ሲሆን፣ ይኸው የብድር መጠን ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ72 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው።

በአሁኑ ወቅት 15.91 ሚሊዮን ደንበኞች ያሉት የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ፣ 22ኛ የባለአክሲዮኖች ዓመታዊ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል።

በኤዶም አማረ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: