አንዲት ሀገር የቱንም ያህል የታሪክ እና የፖለቲካ ሉዓላዊነት ቢኖራትም፣ ኢኮኖሚዋ ጠንካራ ካልሆነ እውነተኛ ከፍታ ላይ መድረስ አትችልም።
የጥንታውያን የፖለቲካ ኢኮኖሚ ምሁራን እንደሚሞግቱት፣ የፖለቲካ ነፃነት በኢኮኖሚ ነፃነት ካልተደገፈ ባዶ ነው። ዛሬ ላይ ዘመናዊ እና ሉዓላዊት ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ በታላቅነት ለማቆም፣ ምርት እና ምርታማነት የሕልውና እና የስትራቴጂ መሠረት የሆኑትም ለዚሁ ነው።
ይህንን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ እና አህጉራዊ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ የጂኦ ፖለቲካ ጫናዎችን ለመቋቋም፣ ግብርናው እና አምራች ኢንዱስትሪው ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።
ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ከሰባት ዓመታት በፊት 335 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ የነበረው ዓመታዊ የሰብል ምርት፣ ዛሬ ላይ 1.3 ቢሊዮን ኩንታል መድረሱ ነው። የዓለም ባንክ እና የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ በታዳጊ ሀገራት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ከራብ መላቀቅ ብቻ ሳይሆን የውጭ ምንዛሬ ክምችትን በማዳን እና የዋጋ ግሽበትን በመቆጣጠር ረገድ የላቀ የማክሮ ኢኮኖሚ ፋይዳ አለው። ስለዚህም ይህ ስኬት ታላቅ የምርት ብዛት ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን በመቻል በራሷ አቅም መቆም የምትችል ትልቅ ሀገር መሆኗን በተግባር ያሳየ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ ገቢ 11.2 ቢሊዮን ዶላር መድረሱ፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 4.5 ቢሊዮን ዶላር ማስመዝገቡ እና የአምራች ኢንዱስትሪው በ15.8 በመቶ ማደጉ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም።
በልማት ኢኮኖሚክስ መርሕ ይህ አኃዝ የሚያመለክተው ኢትዮጵያ ከባህላዊ የግብርና አሠራር ወደ ዘመናዊ መዋቅራዊ ሽግግር እና ገቢ ምርትን ወደ መተካት እያመራች መሆኑን ነው። እነዚህ አኃዞች ምርት እና ምርታማነት የሀገርን ከፍታ እንዴት በተጨባጭ እንደሚያሳድጉ የሚያረጋግጡ ማክሮ ኢኮኖሚያዊ እውነታዎች ናቸው።
ኢትዮጵያ እንደ ትልቅ ሀገር ከፍታዋን እያረጋገጠች ያለችው በቁጥር ዕድገት ብቻ ሳይሆን፣ ሥራን በቅጡ የመከወን እና ውጤታማ የማድረግ አዲስ የትግበራ ልማድ እና የመፈጸም አቅም በመፍጠሯ ጭምር ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ ተምሳሌት እየተጠቀሱ ያሉት የከተሞች ኮሪደር ልማት እና የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሮች የሀገራችንን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ፣ በዜጎች ዘንድ ትልቅ የሥነ ልቦና ከፍታን እና የመፈጸም አቅምን አምጥተዋል።
በምጣኔ ሀብት ምሁራን ዕይታ እንዲህ ያሉ ግዙፍ የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንቶች ለግሉ ዘርፍ የካፒታል ዝውውር እንደ ማነቃቂያ ያገለግላሉ። ይህ ጥልቅ ሐሳብን መሠረት ያደረገ የመፈጸም አቅም፣ ያልታሰቡ አደጋዎችን ለመከላከል የሚያስችል ብሔራዊ ዕሴት ሆኗል።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ ለሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ባደረጉት ንግግር ለ2019 ዓ.ም ያስቀመጧቸው የትኩረት አቅጣጫዎችም ይህንኑ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አጠንክረው የሚያስቀጥሉ ናቸው።
ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መጠበቅ፣ የኢንዱስትሪ እና የግብርና ግብዓቶችን በራስ አቅም መሸፈን ወሳኝ መሆናቸውን መጥቀሳቸው ይታወቃል። በዚህም አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገቱን 10.1 በመቶ ለማድረስ ሰፊ ርብርብ ይደረጋል።
ይሁንና ይህንን ታልቅ ሀገራዊ ራዕይ ይበልጥ ለማጽናት እና ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ጥቂት ወሳኝ የፖሊሲ እና የተግባር እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል። ከነዚህም መካከል የተመዘገበውን የግብርና ምርት በጥሬው ከማቅረብ ይልቅ በቴክኖሎጂ በማገዝ ወደ አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች የበለጠ ማሸጋገር እና የእሴት ሰንሰለቱን ማስፋት በዋናነት ይጠቀሳል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የካፒታል ፍሰት እና ኢንቨስትመንት መረጋጋትን ስለሚፈልግ፣ ሀገራዊ ሰላምን በዘላቂነት ማረጋገጥ የኢኮኖሚ ፖሊሲው ዋነኛ አካል መሆን ይኖርበታል። በተጨማሪም እንደ አፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ያሉትን ሰፊ የገበያ ዕድሎች ለመጠቀም የምርት ተወዳዳሪነትን ማሳደግ፣ አስተማማኝ የባሕር በር እና የሎጂስቲክስ አማራጮችን በዲፕሎማሲ ማስፋት እንዲሁም ሙስናን እና ቢሮክራሲያዊ ማነቆዎችን በዲጂታይዜሽን መፍታት የነገ የማይባሉ የቤት ሥራዎች ናቸው።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና የትልቅ ሀገርነት ክብር የሚረጋገጠው ማሳችን ሲሞላ፣ ፋብሪካዎቻችን ሲያመርቱ እና የሕዝባችን ተጠቃሚነት ሲረጋገጥ ነው። ምርትና ምርታማነት የዕለት ተዕለት የኢኮኖሚ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ዘላቂ ከፍታዋን ጠብቃ እንድትራመድ የሚያደርጋት ጽኑ ምሰሶ ነው።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: