Search

የኢትዮጵያውያን የጽናት፣ አንድነትና ብሔራዊ ልህቀት የሕገ ወጡ ህወሓትን ሀገር የማፍረስ አሻጥሮች አክሽፏል

ሰኞ ጥቅምት 09, 2019 60

በ1960ዎቹ አጋማሽ በደደቢት በረሃ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ የሕገወጡ ህወሓት ዋና የፖለቲካ ባህሪ ሀገርን የመሸጥ፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ የመስጠትና ለሕዝቦች የጋራ ህልውና ደንታ ቢስ የመሆን ስነ-ልቦናዊና ፖለቲካዊ ማንነት እንደሆነ የታሪክ ማህደሮች፣ ሰነዶችና የቀድሞ የቡድኑ አባላት ምስክርነት ያረጋግጣሉ።

አንድን የፖለቲካ ቡድን ከሌሎች የሚለየው ለቆመለት ሀገር ያለው ታላቅ ራዕይ ቢሆንም የሕገወጡ ህወሓት ራዕይ ግን ኢትዮጵያን ማዳከምና ማፍረስ ላይ የተመሠረተ እንደነበር ይገለጻል።

ይህ የፀረ-ኢትዮጵያዊነት አካሄድ በ1967 ዓ.ም በወጣው የፖለቲካ ማኒፌስቶው ላይ በግልጽ የሰፈረ ሲሆን፣ ዋነኛ ዓላማውም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ሳይሆን ከሀገር ተገንጥሎ "ታላቋን የትግራይ ሪፐብሊክ" መመስረት እንደነበር ይነገራል።

የቀድሞው የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ሀብቱ ኪሮስ እንደሚያስረዱት ቡድኑ በ1968 ማኒፌስቶው ትግራይን ነፃ ማውጣትና እንደ ሀገር የማቆም ዓላማ የነበረው ሲሆን በኋላ ላይ "በእኩልነት ላይ የምትገነባ ሀገር" የሚል ሀሳብ ቢያመጣም፣ ስልጣን ባጣበትና በፈለገበት ወቅት ሀገር የማፍረስ ስራውን እውን ለማድረግ ለሀገር ጥቅም ስትራቴጂካዊ ጉዳት የሚያስሱ ኃይሎችን የመሰብሰብ ስልት ይከተላል።

ሕገ ወጡ ህወሓት በ1983 ዓ.ም የመንግሥት ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላም ቢሆን የሀገርን የረጅም ጊዜ ብሔራዊ ጥቅም እና የጂኦፖለቲካ የበላይነት ወደ ጎን በመተው ኢትዮጵያ ከባህር በር እንድትርቅ በማድረግ የታሪካዊ ጠላቶችን ፍላጎት አሳክቷል።

በተጨማሪም ህገ ወጡ ህወሓት የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም ሲል ኢትዮጵያዊነትን እንደ ትምክህትና የአፈና መሳሪያ አድርጎ በመሳል፣ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ቅርሶችና የጋራ እሴቶች በፕሮፓጋንዳ ማሽኑ ሲያብጠለጥል ኖሯል።

የስምረት ፓርቲ አባል አቶ ጣዕመ አረዶም እንደሚያስረዱት፣ ህገወጡ ህወሓት ህዝቡን በራሱ መንገድ ብቻ ለመንዳት ለ50 ዓመታት የሰራ ሲሆን፣ የተለየ ሀሳብ የሚያመጡ ዜጎችን በማፈንና በማጥፋት ከባድ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ሲፈጥር ቆይቷል።

የመንግሥት ተቋማትንም የሀገር የጋራ ቤት ከማድረግ ይልቅ የቡድኑን የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነት ማረጋገጫ እንዲሁም የሀገር ሀብት ዘረፋ ማመቻቻ አድርጎ አዋቅሯቸዋል።

ሆኖም ግን ህገ ወጡ ህወሓት ከፅንሱ ጀምሮ ያሳየው ወጥ የሆነ አፍራሽ ባህሪ ለኢትዮጵያ ህልውና ደንታቢስ መሆን ቢሆንም፣ የቡድኑን ፀረ-ኢትዮጵያዊነት የተረዱ ኢትዮጵያውያን ግን በጽናት ታግለውታል።

በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባው የኢትዮጵያውያን አንድነትና የሀገር ፍቅር ትስስር በቀላሉ የማይበጠስ መሆኑን ያስመሰከሩት ዜጎች፣ ዛሬ ላይ ከራስ በላይ ሀገርን የሚያስቀድሙ ጀግኖችን በማፍራትና ሀገራዊ ተቋማትን የሉዓላዊነትና የብሔራዊ ጥቅም አስተማማኝ ጋሻ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

ይህ የሕዝቦች ድልና የጽናት ጉዞ ኢትዮጵያ በፅኑ መሠረት ላይ የተገነባች #ትልቅሀገር፣ የታሪካዊ አሻጥሮችን ሴራ ያከሸፈ #ትልቅሕዝብ እና ለነገው ዘመን የተዘረጋ #ታላቅርዕይ ያላት ሀገር መሆኗን በግልጽ ያረጋገጠ ነው።

በላሉ ኢታላ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: