በምስራቅ አፍሪካ እና በዓባይ ተፋሰስ የጂኦፖለቲካ ምህዳር ውስጥ የኢትዮጵያ የልማትና የሉዓላዊነት ጉዞ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ ሲመጣ፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለጠቅላላው አፍሪካ የታደለ የታሪካዊ አህጉራዊ ሀብት ማረጋገጫ ሆኖ ተመዝግቧል።
የካይሮ አስተዳደር የቀጣናውን የውሃ ሀብት እና የባህር በር ፍላጎቶች በብቸኝነት ለመቆጣጠር የሚያደርገው የዘመናት እኩይ ሴራ በህጋዊ፣ በፖለቲካዊ እና በኢኮኖሚያዊ እውነታዎች ሙሉ በሙሉ ከሽፏል።
በዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ዙሪያ ለዘጠኝ አስርት ዓመታት በላይ ሲካሄድ የቆየው ውዝግብ አዲስ አህጉራዊ ምዕራፍ ላይ የደረሰ ሲሆን፣ በ1929 እና በ1959 በቅኝ ግዛት ውሎች ተመስርተው የናይልን ውሃ ለሁለት አገራት ብቻ የከለሉት አግላይ ስምምነቶች በአህጉራዊው የትብብር ማዕቀፍ (CFA) ስራ ላይ መዋል ሙሉ በሙሉ ተሽረዋል።
ኢትዮጵያ ባልተሳተፈችባቸውና ባልተቀበለችባቸው የቅኝ ግዛት ውሎች ልትገደድ እንደማትችል እና የውሃ ሀብቷን የማልማት ተፈጥሯዊ መብቷ በዓለም አቀፍ የውሃ ሕግ የተረጋገጠ መሆኑ፣ የካይሮን የቆየ የይገባኛል ጥያቄ ከታሪክ ቅሪትነት ያለፈ ዋጋ የሌለው አድርጎታል።
የግብፅ መሪዎች በቅኝ ግዛት ዘመን የተደረጉ አግላይ ስምምነቶች በድንጋይ ላይ እንደተጻፉ የማይለወጡ እና ዘላለማዊ እንደሆኑ በሚቆጥር የኋላ ቀር አስተሳሰብ ተጠምደው ይገኛሉ።
ሁኔታዎች፣ የአካባቢ ጥበቃ ፍላጎቶች እና የቀጠናዊ ልማት ነባራዊ እውነታዎች በከፍተኛ ሁኔታ ቢቀየሩም፣ ከቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶች ጋር ተጣብቆ የመቆየት ፍላጎት በካይሮ በኩል ይስተዋላል።
ይሁን እንጂ ማንኛውም የፖለቲካና የህግ ለውጥ በዓባይ ውሃ ላይ እከተለዋለሁ በሚለው የቅኝ ግዛት የበላይነት ላይ መሰረታዊ ሽረትን የሚያስከትል በመሆኑ፣ ካይሮ ከተቀየረው አህጉራዊ እውነታ ጋር መላመድ ተስኗታል።
በአንጻሩ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በዋናነት ኤሌክትሪክ ለማመንጨትና የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ለመደገፍ ታስቦ የተገነባ ግዙፍ ኢንቨስትመንት በመሆኑ፣ ፋይዳው ከሀገራዊ ወሰን አልፎ የመላው አፍሪካ አህጉር የጋራ የልማት ምሰሶ እና የኢኮኖሚ ትስስር አቅም ሆኖ አገልግሏል።
ኢትዮጵያ ከውሃ ኃይል የምታመነጨውን ታዳሽ ኤሌክትሪክ ለኢንዱስትሪ፣ ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለግብርና ልማት እና ለሥራ ዕድል ፈጠራ በመጠቀም ለአህጉራዊ ትስስር እውን መሆን የፊት አውራሪነቱን ሚና እየተወጣች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ ለኬንያ፣ ለጂቡቲ፣ ለታንዛኒያ እና ለሌሎችም ቀጣናዊ አጋሮች የምታደርገው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ፣ የኃይል መሠረተ ልማት የቀጣናውን የኢኮኖሚ ትስስር ለማጠናከር ያለውን ግዙፍ አቅም በተግባር ያረጋገጠ ነው።
ይህ የታደሰ ታሪካዊ እመርታ ሀገራችን በፅኑ መሠረት ላይ የቆመች #ትልቅሀገር፣ የጋራ እድገትን የታጠቀ #ትልቅሕዝብ እና ለአህጉሩ የተዘረጋ #ታላቅርዕይ ያላት ሀገር መሆኗን በተግባር ያረጋገጠ ነው።
የኤሌክትሪክ ኃይል የኢኮኖሚ እድገት ዋና ሞተር በመሆኑ፣ ይህ አቅርቦት ማደጉ ግብፅንና ሱዳንን ጨምሮ በመላው የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ውስጥ ሰፊ የኢኮኖሚ ዕድሎችን፣ የግብርና ልማትን፣ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን እና የዳታ ማዕከላትን የማስፋፋት አቅም ይፈጥራል።
ሆኖም ግን የግብፅ መሪዎች ይህንን ተራማጅና አህጉራዊ የጋራ የልማት እድል ከመደገፍ ይልቅ ኢትዮጵያን በወታደራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ ወይም በፖለቲካዊ ጫና ለማዳከም እና የቀጣናውን ሰላም ለማወክ ያለመ የከሸፈ ፖሊሲ ሲከተሉ ይስተዋላል።
ሽብርተኝነትን በመደገፍ የተለያዩ አሻጥር አክቲቪስቶችንና አገራትን በመጠቀም እንዲሁም መሳሪያዎችን በማቅረብ ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ ለማድረግ የሚደረጉ ሙከራዎች በሙሉ የኢትዮጵያን አገራዊ ቁርጠኝነትና የህዝቦቿን አንድነት ማፍረስ አልቻሉም።
ኢትዮጵያን በጫና ለማስገደድ የሚደረጉ ማንኛቸውም እንቅስቃሴዎች የማይሳኩ መሆናቸውን የተገነዘበው አህጉራዊው ማህበረሰብ፣ ግብፅ የተሳሳተና የቆየ የቅኝ ግዛት ፖሊሲዋን በመመርመር፣ ከማደናቀፍ ወጥታ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ብልጽግና፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በቀጣናዊ ትስስር ላይ የተመሰረተ እውነተኛ የኢኮኖሚ ትብብር እንድታደርግ ግፊት ማድረግ አለበት።
በዓባይ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ የነበረው አግላይና ፍትሐዊ ያልሆነ የቅኝ ግዛት አሰራር መታቀፉ እና የተፋሰሱ አገራት በጋራና በእኩልነት የሚጠቀሙበት የትብብር ማዕቀፍ (CFA) መዘርጋቱ፣ የቀጣናውን የኃይል ሚዛን ለዘላቂ ልማት የሚለውጥ ትልቅ አህጉራዊ እመርታ ነው።
የግብፅ የዘመናት ሴራዎች እና ወታደራዊ ስጋቶች የኢትዮጵያንና የሌሎችን የተፋሰስ አገራት የልማት ርምጃ ማስቆም አልቻሉም።
ካይሮ ከውሸት ትረካና ከብቸኛ የይገባኛል ጥያቄ ወጥታ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመላው አፍሪካ አህጉር የጋራ ሀብት አድርጋ በመቀበል፣ በጋራና በፍትሐዊ የሀብት አጠቃቀም መርህ ላይ በተመሠረተ ሁለንተናዊ ትብብር ላይ መሰለፍ ብቻ የቀጣናውን ዘላቂ ሰላም እና አህጉራዊ ብልጽግና ማረጋገጥ የሚችል ስትራቴጂካዊ መንገድ ነው።
በሰለሞን ገዳ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: