ጤና ማኅበራዊ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ የኢኮኖሚ ልማት፣ የመረጋጋት እና የደኅንነት መሠረት መሆኑን የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ገልጸዋል።
በአፍሪካ የሕዝብ ጤና ላይ ያተኮረውን 5ኛ ዓለም አቀፍ የአፍሪካ ሕዝብ ጤና ጉባኤ ኢትዮጵያ በማስተናገዷ ምስጋና ያቀረቡት ሊቀመንበሩ፣ አፍሪካ የጤና ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ ግልጽ ዓላማ ይዛ እየተንቀሳቀሰች እንደምትገኝ ጠቅሰዋል።
የቅርብ ጊዜ የጤና ቀውሶች እና የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድጋፎች መቆራረጥ አኅጉሪቱ ለውጫዊ አደጋዎች ያላትን ተጋላጭነትና የብሔራዊ የጤና ሥርዓቶችን ደካማነት ማሳየቱን አመላክተዋል።
የጤና ሥርዓት በውጭ ሀብትና በሌሎች በጀቶች ላይ ብቻ በዘላቂነት መመሥረት እንደማይቻል ገልጸው፣ አፍሪካ የራሷን ኃላፊነት መውሰድ እንደሚገባት አጽንኦት ሰጥተዋል።
ባለፈው የካቲት ወር በተካሄደው 39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የጤና ደኅንነት እና ሉዓላዊነት አጀንዳ መጽደቁን እና በሐምሌ 2026 በአክራ በተካሄደ ልዩ ስብሰባም እስከ 2030 የሚተገበረው የአክራ መግለጫ መጽደቁን አስታውሰዋል።
ወደ ተግባር ለመሸጋገር አራት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች መለየታቸውን አንስተው፣ የጤና ዘርፍ የገንዘብ ድጋፍን ማጠናከር፣ የሚያስፈልጉ የጤና ምርቶችን በአፍሪካ ማምረት፣ የጤና ቀውሶችን አስቀድሞ ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የጋራ አቅም መገንባት እንዲሁም ቃል ኪዳኖችን ወደ ተጨባጭ ውጤት መለወጥ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ማለት የሕፃናት ክትባት፣ የነፍሰ ጡሮች ክትትል፣ የጎልማሶችም ሕክምና ማግኘት መቻላቸው እንደሆነ ገልጸዋል።
የ2026ቱ የአፍሪካ ኅብረት መሪ ሐሳብ ውኃ እና ንጽሕና ጥበቃ መሆኑን ጠቅሰው፣ የጤና ጥበቃ በሆስፒታሎች ብቻ እንደማይጀምርና ንጹሕ አካባቢ፣ የምግብ ዋስትናና ትምህርት የሂደቱ አካል መሆናቸውን ገልጸዋል።
አባል ሀገራት የጤናን ዘርፍ እንደ ትምህርት፣ ደኅንነት እና ፍትሕ ዘርፍ ቅድሚያ እንዲሰጡት፣ አጋሮችም ዕቅዶቻቸውን ከአፍሪካ ቅድሚያዎች ጋር እንዲያጣጥሙና የምርምር ተቋማት በገንዘብ እንዲደገፉ ጥሪ አቅርበዋል።
በመሀመድ ፊጣሞ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: