Search

የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነት ስላበቃ ብቻ የታካሚው ሕክምና መቋረጥ የለበትም፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ሰኞ ኅዳር 14, 2019 6

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው 5ኛው የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባዔ ጉባኤን በንግግር ከፍተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፣ የአፍሪካ የጤና ሉዓላዊነት እና ደኅንነት የሚረጋገጠው በራስ አቅም በተገነባ እና ዘላቂነት ባለው የጤና ሥርዓት መሆኑን አስገንዝበዋል።

አንድ ታካሚ የሚያገኘው ሕክምና የውጭ የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት ስላበቃ ብቻ መቋረጥ እንደሌለበት በአጽንኦት ገልጸዋል።

ለዜጎች ጤና የሚደረግ ጥበቃ ታካሚዎች ወደ ጤና ተቋማት ከመድረሳቸው አስቀድሞ በንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ በተመጣጠነ ምግብና ለሕፃናት ምቹ የመኖሪያ አካባቢን በመፍጠር እንደሚጀምር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ለበሽታዎች መስፋፋት ምክንያት በመሆኑ ጤናን የመንግሥት አስተዳደር እና የኢንቨስትመንት ዋነኛ ማዕከል ማድረግ መቻሉንም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ በአብዛኛው በሴቶች የሚመራው የጤና ኤክስቴንሽን መርሐ ግብር በማኅበረሰቡ ውስጥ አመኔታን በማትረፍ መሠረታዊ የጤና አገልግሎቶችን ወደ እያንዳንዱ ቤተሰብ ማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል።

ቤተሰቦችን ከድንገተኛ የሕክምና ወጪ ጫና ለመታደግም በባህላዊ የመረዳዳት እሴት ላይ የተመሠረተው የጤና መድን ሽፋን እየተስፋፋ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የመድኃኒት እና የክትባት ፍላጎቷን በሀገር ውስጥ ለመሸፈን በኢንዱስትሪ ፓርኮች ሰፊ ሥራ እያከናወነች መሆኗን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ባለፈው ዓመት በመድኃኒት እና ክትባት ቁጥጥር ረገድ የዓለም ጤና ድርጅትን የብቃት ደረጃ 3 (WHO Maturity Level 3) ማሳካቷ ለሀገር ውስጥ አምራቾችና ለቀጣናው ትልቅ አቅም መፍጠሩን አስታውቀዋል።

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: