የተገባደደው 2025 የፈረንጆች ዓመት ግብርናን በሰው ሰራሽ አስተውሎት በመደገፍ ረገድ ትልቅ የቴክኖሎጂ እመርታ የታየበት እና ግብርናን የሚያዘምኑ በርካታ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ይፋ የተደረጉበት ነው።
ከነዚህም አንዱ የሰው ልጅ ለዘመናት ሲጠቀምባቸው የቆዩትን የአረም ማጥፊያ ኬሚካሎች ይተካል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት አዲስ ቴክኖሎጂ ነው።

በቻይናው የቴክኖሎጂ ኩባንያ Huagong ይፋ የተደረገው Laser Weeder የተባለው ትራክተር መሰል መሳሪያ አረምን ለማጥፋት ኬሚካልን ሳይሆን ብርሃንን የሚጠቀም ነው።
ይህ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚታገዘ ሮቦት በሰከንድ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ አረሞችን ከተክሎች ለይቶ ለሰው ልጅ ጎጂ ባልሆነ ሌዘር ብርሀን የመምታት አቅም ያለው ነው።
በአንድ ሰዓት ውስጥ እስከ 320 ሺህ አረሞችን በማጥፋት የኬሚካል አጠቃቀምን መቶ በመቶ እንደሚያስቀር ታምኖበታል።

ባሳለፍነው የፈረንጆች ዓመት ግብርናን ለማዘመን ይፋ ከተደረጉ የቴክኖሎጂ ግኝቶች መካከል ሌላው አስገራሚ የተባለው የሮቦት ንቦች ጉዳይ ነው።
እነዚህ ረቂቅ ሮቦት ንቦች የተፈጥሮ ንቦች በማይደርሱባቸው የቤት ውስጥ እርሻዎች ውስጥ ዘርን በማዳቀል ረገድ ትልቅ መፍትሄ እንደሚሆኑ ይጠበቃሉ።
በመጠናቸው ከእውነተኛ ንቦች ጥቂት የሚበልጡት እነዚህ ሮቦት ንቦች ከተፈጥሯዊ ንቦች ጋር ተቀላቅለው በአበቦች መካከል እየበረሩ የአበባ ዱቄት የማስተላለፍ (Pollination) ሥራን እንዲያከናውኑ ተደርገው የተሠሩ ናቸው።
ሮቦት ንቦቹ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በሚገባ በመፈፀም ረገድም ውጤታማ መሆናቸውን አስመስክረዋል።
የተፈጥሮ ንቦች ቁጥር መቀነስ ያስከተለውን ስጋት ለመቅረፍ በዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ይፋ የተደረጉትን የእነዚህን ጥቃቅን ሮቦቶች በተለይ ከባትሪ ጋር በተገናኘ አቅማቸውን ለማጎልበት ምርምሩ እንደቀጠለ ነው።
ይህ ሲጠናቀቅ ሮቦት ንቦቹ በተፈጥሮ ንቦች እጥረት ምክንያት ሊያጋጥም የሚችለውን የምርት መቀነስ ለማካካስ ያስችላሉ በሚል ተስፋ ተጥሎባቸዋል።

በተለይ በረሀማ ለሆኑ አካባቢዎች ታላቅ የምስራች ይዞ የመጣው የኖርዌይ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ግኝትም ከ2025 የግብርና ቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ዋንኛው ነው።
Desert Control የተሰኘው ይህ ቴክኖሎጂ በተለይ በረሃማነትን ለመዋጋት ለሚጥሩ ሀገራት ትልቅ ብስራት ሆኗል።
ኩባንያው Liquid Nanoclay (LNC) በተሰኘ ፈሳሽ ቴክኖሎጂ በረሀማ የሆነን መሬት፣ ሊታረስ ወደሚችል ለም መሬት መቀየር እንደሚቻል ይፋ አድርጓል።
ኩባንያው አዲስ እና ርካሽ እንደሆነ የተነገረለትን ይህን ቴክኖሎጂ ለዱባይ እና ለሳውዲ አረቢያ ገበሬዎች በይፋ አስተዋውቋል።
በዚህም ቴክኖሎጂው ደረቅ እና አሸዋማ መሬትን በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ለም ወደሆነ የእርሻ መሬት በመቀየር የተዘራበት ዘር እንዲበቅል ማስቻሉ ተረጋግጧል።
Liquid Nanoclay የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ፈሳሽ ንጥረ ነገር በተፈጥሮ ሂደት ከ7 እስከ 15 ዓመታት የሚፈጀውን አፈርን የማበልጸግ ሂደት ወደ 7 ሰዓታት ብቻ በማሳጠር በረሀማ ቦታዎችን ወደለምነት መቀየር አስችሏል።
ከዚህ በመነሳትም ቴክኖሎጂው በሳውዲ አረቢያ በረሃማነትን ለመከላከል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዛፎችን ለመትከል እንደ ዋና መሳሪያ ሆኖ ማገልገል መጀመሩ ታውቋል።

በተገባደደው 2025 ተሰርተው ይፋ ከተደረጉ የግብርና ቴኖሎጂዎች መካከል ሌላው አስገራሚው ግኝት በሰው ሰራሽ አስተውሎት በመታገዝ ያለአንዳች የሰው እርዳታ የእርሻ ሥራን የሚያቀላጥፈው ስማርት ትራክተር ነው።
በዕድሜ ጠገቡ የአሜሪካ የግብርና መሳሪዎች አምራች ኩባንያ ጆን ዲር ተሞክሮ ውጤታማ የሆነው Autonomous 9RX ትራክተር፣ በላዩ ላይ በተገጠሙለት 16 ካሜራዎች እና በAI ታግዞ ያለ ሰው እርዳታ የተሰጠውን ማሳ በሚገባ ማረስ እና መዝራት እንደሚችል አስመስክሯል።
ይህ ሰው አልባ የእርሻ ትራክተር በተለይ የሰው ኃይል እጥረት ባለባቸውና ምቹ ባልሆኑ አካባቢዎች የሰውን ልጅ ተክቶ የእርሻ ሥራዎችን ያከናውናል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

ግብርናን ለማዘመን እና ምርታማነትን ለማሳደግ በጥቅም ላይ መዋል ከጀመሩ ግኝቶች መካከል ሌላው በላሞች አንገት ላይ የሚታሰረው Smart Collar ነው።
የወተት ምርት ኢንዱስትሪውን ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግር የሚጠበቀው ይህ የአንገት ማሰሪያ ቴክኖሎጂ፣ በተለይ በትልልቅ አርሻዎች ውስጥ የእንስሳትን ጤና ለመከታተል ጭምር የሚጠቅም ነው።
ይህ ቴክኖሎጂ አንዲት ላም የምትመገበውን ምግብ የምታመሰካበትን ፍጥነት እና የምግብ መፈጨት ሂደቷን በቀጥታ በመከታተል መረጃውን ወደ አርቢዋ ስልክ ያስተላልፋል።
የላሚቱ የምግብ መፈጨት ፍጥነት ከቀነሰ በሰው ሰራሽ አስተውሎት አማካኝነት የጤናዋን ሁኔታ በመተንበይ የሕመም ምልክት ከመታየቱ አስቀድሞ ለአርቢዋ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል።
በተጨማሪም ይህ አዲስ ቴክኖሎጂ በጤናዋ እና በአመጋገቧ ላይ በመመስረት አንዲት የወተት ላም በቀን ስንት ሊትር ወተት እንደምትሰጥ አስቀድሞ የመተንበይ አቅም አለው።
በተመሳሳይ ቴክኖሎጂው አንዲት ላም ለመራባት ዝግጁ የምትሆንበትን ጊዜ 99 በመቶ በትክክል በመለየት የእርባታ ሥራን ውጤታማ ያደርጋል።
በጥቅሉ ያሳለፈነው 2025 የፈረንጆች ዓመት የሰው ልጅን ድካም እንደሚያቀልሉ እንዲሁም ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ የዓለማችንን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እንደሚያስችሉ የታመነባቸው ብዛት ያላቸው ቴክኖሎጂዎች ይፋ የሆኑበት እና በስፋት ተመርተው ገበያ ላይ እንዲውሉ ወደ ሥራ የተገባበት ዓመት ሆኖ አልፏል።
በዋሲሁን ተስፋዬ
#EBC #ebcdotstream #outgoing2025 #smartfarming #technology #inventions