Search

በአማራ ክልል የሰላም አማራጭን የተቀበሉ የቀድሞ የመንግሥት ሠራተኞች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ተወሰነ

ሓሙስ የካቲት 19, 2018 62

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መስተዳድር ምክር ቤት የሰላም አማራጭ ተቀብለው የተመለሱ እና በተለያዩ የመንግሥት መዋቅር ስር ሲያገለግሉ የነበሩ የቀድሞው የመንግሥት ሰራተኞች ወደ መንግሥት ስራቸው እንዲመለሱ ውሳኔ አሳልፏል።

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መስተዳድር ምክር ቤት 6 ዙር፣ 5 ዓመት የሥራ ዘመን 8 መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።

ምክር ቤቱ በስብሰባው የሰላም አማራጭን ተቀብለው በተመለሱና ቀደም ሲል በተለያዩ የመንግሥት መዋቅሮች ሲያገለግሉ በነበሩ ሠራተኞች ላይ ውሳኔ አሳልፏል።

የክልሉ መንግሥት ሰላምን ለማጽናትና ልማትን ለማረጋገጥ ባለው ጽኑ ቁርጠኝነት፣ ታጥቀው ለሚንቀሳቀሱ አካላት በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ሲያቀርብ መቆየቱ ይታወሳል።

በዚህም መሠረት በመንግሥት ጥሪ፣ በድርድርና በውይይት የሰላም አማራጭን መርጠው የተመለሱና የተሃድሶ ሥልጠና የወሰዱ የቀድሞ የመንግሥት ሠራተኞች ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲመለሱ ምክር ቤቱ ወስኗል።

ይህ ውሳኔ የክልሉ መንግሥት ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታትና ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ያለውን ዝግጁነት የሚያሳይ መሆኑ ተገልጿል።

በቀጣይም ለክልሉ ዕድገትና አንድነት መሰል የሰላም ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተመላክቷል።

በራሄል ፍሬው

#EBC #Ethiopia #AmharaRegion #PeaceProcess #CivilService #NationalUnity #PeaceInitiative