Search

ዚምባብዌን ጨምሮ አምስት ሀገራት ለተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ተመረጡ

ሓሙስ ግንቦት 27, 2018 94

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ አፍሪካዊቷን ዚምባብዌን ጨምሮ ኦስትሪያ፣ ኪርጊዝስታን፣ ፖርቹጋል፣ እንዲሁም ትሪኒዳድ እና ቶቤጎን ከጥር 1 ቀን 2027 ጀምሮ ለሁለት ዓመታት የሚያገለግሉ የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ያልሆኑ አባላት አድርጎ ረቡዕ ዕለት መርጧል።

በአህጉራዊ ውክልና መሠረት ዚምባብዌ ሌላኛዋን የምሥራቅ አፍሪካ ሀገር ሶማሊያን የምትተካ ሲሆን፤ በአንጻሩ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ላይቤሪያ ከባህሬን፣ ኮሎምቢያ እና ላቲቪያ ጋር በመሆን እስከ 2027 ማብቂያ ድረስ የአፍሪካንና የሌሎች ቀጠናዎችን ድምፅ በምክር ቤቱ ማስተጋባታቸውን ይቀጥላሉ። 

በዚህ ታሪካዊ ምርጫ ወቅት መቀመጫውን ለማግኘት ጠንካራ ቅስቀሳ ስታደርግ የነበረችው ጀርመን 104 ድምፅ ብቻ በማግኘት ከውድድሩ ውጪ ስትሆን፥ ፖርቹጋል 134 ድምፅ እንዲሁም ኦስትሪያ 131 ድምፅ ከምዕራብ አውሮፓ እና ሌሎች ቡድን የተመደቡትን ሁለት ወንበሮች አሸንፈዋል።

 

ለእስያ-ፓስፊክ ቡድን ወንበር በፊሊፒንስ እና በኪርጊዝስታን መካከል የተደረገው ብርቱ ፉክክር እስከ አራት ዙር የዘለቀ ሲሆን፥ በመጨረሻም ኪርጊዝስታን ፓኪስታንን ለመተካት የሚያስችላትን ታሪካዊ የመጀመሪያ የጸጥታው ምክር ቤት ወንበር 142 49 ድምፅ አረጋግጣለች።

ማዕቀብ የመጣልና የኃይል እርምጃ የመፍቀድ ሕጋዊ አስገዳጅነት ያለው ውሳኔ የሚያሳልፈው ይህ 15 አባላት ምክር ቤት፥ አምስት የቪቶ መብት ያላቸው ቋሚ አባላት (ብሪታንያ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ እና አሜሪካ) ያሉት ሲሆን የቀሩት 10 አባላት ግን በየዓመቱ አምስት አዳዲስ አባላት እየተተኩ የሚመረጡ ናቸው።

በዚህም መሠረት አዲሶቹ ተመራጮች ትሪኒዳድ እና ቶቤጎ ፓናማን፣ ፖርቱጋል እና ኦስትሪያ ደግሞ ዴንማርክንና ግሪክን ይተካሉ።

በሌላ በኩል የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ማክሰኞ ዕለት ባካሄደው ምርጫ የባንግላዲሽን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካሊሉር ራህማንን በመስከረም ወር ለሚጀምረው 81ኛው የጉባኤው ክፍለ-ጊዜ ፕሬዝዳንት አድርጎ መምረጡን ሮይተርስ ዘግቧል።

በመሐመድ ፊጣሞ