Search

ኢትዮጵያውያን ሁሉ ልትኮሩበት የሚገባ ሥራ ነው የሰራችሁት፦ ኡሁሩ ኬንያታ

ሓሙስ ግንቦት 27, 2018 37

የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ እና የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት መጠናቀቁን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ በመግለጫቸው የምርጫው ሂደት መጠናቀቅ የኢትዮጵያን የታሪክ ልዕልና እና የዴሞክራሲ ጉዞ ዳግም ያረጋገጠ መሆኑን ገልጸው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ ስኬት ሊኮራ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

73 አባላት ያሉት የታዛቢ ቡድን መሪው ኡሁሩ ኬንያታ፣ ኢትዮጵያውያን ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያሳዩት ቁርጠኝነት የታሪክ አሻራቸውን የሚያሳድስ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ማዕበል ፊት በአንድነት በመቆም ያልተገዛች ሀገር መሆኗን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፣ ይህ ታሪካዊ ፅናት ሊታወስ እንደሚገባ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነፃነት እና አፍሪካውያን ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብታቸው እንዲከበር በፅናት የቆመች ሀገር በመሆኗ የአፍሪካ መዲና ለመሆን መብቃቷን አስታውሰዋል፡፡ 

አሁንም ይህንን የታሪክ አደራ በዴሞክራሲያዊ ሂደት እያሳደሰችው እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ምርጫውን በስኬት በማካሄዷ በአህጉሪቱ ያላትን የሞራል የበላይነትና የታሪክ አሻራ በድጋሚ ማረጋገጧን የጠቀሱት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ይህም ለኢትዮጵያውያን የኩራት ምንጭ ሊሆናቸው እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ 

ይህ የምርጫ ሂደት ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን ኩራትና ራሳቸውን በራሳቸው የመምራት መብታቸው መከበር ዋስትና ሆና መቆየቷን በድጋሚ ያበሰረ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በላሉ ኢታላ