አሜሪካ እና ኢራን በሰላም ድርድሩ ማዕቀፎች ላይ መስማማታቸውንና የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነቱን በ24 ሰዓታት ውስጥ እንደሚፈራረሙ ፓኪስታን አስታወቀች።
የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሻህባዝ ሻሪፍ ከሦስት ወር በላይ የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም የሚያስችለው የመጀመሪያ ደረጃ የሰላም ስምምነት በሚቀጥሉት 24 ሰዓት ውስጥ አንደሚፈረም ገልጸዋል።
የፊርማ ሥነ ሥርዓቱ በኤሌክትሮኒክስ እንደሚሆን ገልጸው፣ በሚቀጥለው ሳምንት የሁለቱ ሀገራት ባለሥልጣናት ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚያደርጉ መናገራቸውን የቲአርቲ ዘገባ አመላክቷል።
አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር የሚያደርጉትን ጦርነት በዘላቂነት ለማስቆም የሚያስችል የተኩስ አቁም ስምምነት ከምንጊዜውም በላይ መቃረቡን የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ቀደም ሲል መግለጻቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
ስምምነቱ ሁለት ዋና ዋና ምዕራፎች እንዳሉ የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ የመጀመሪያው ምዕራፍ ጦርነቱ በአስቸኳይ የሚቆምበት እና ጥቃቶች ዳግም እንዳይከፈቱ ዋስትና የሚሰጥበት የመግባቢያ ሰነድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ የኢራን የኑክሌር ፕሮግራም ዕጣ ፈንታ የማዕቀቦች መነሳት እና የታገዱ የኢራን ሃብቶች በሚለቀቁበት ሁኔታ ላይ የሚደረግ ዝርዝር ድርድር መሆኑን አመልክተዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አዲሱ ስምምነት በዚህ ሳምንት መጨረሻ ሊፈረም እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
አሜሪካ ስምምነቱ በፍጥነት ይፈረማል ብትልም በኢራን በኩል ግን ሰነዱ ወደ ፊርማ ከማምራቱ በፊት በጦር ኃይሉ፣ በፓርላማው እና በጠቅላይ መሪው በኩል ታይቶ ሀገራዊ የጋራ ስምምነት ላይ መድረስ ስለሚያስፈልግ ሂደቱ ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ተዘግቧል።
ትራምፕ የኢራንን ካርግ ደሴት ለመቆጣጠር ዝተው የነበረ ቢሆንም፣ በስምምነቱ ተስፋ ምክንያት ሦስተኛውን ዙር የአሜሪካ ጥቃት መሰረዛቸው ይታወሳል።
በቢታኒያ ሲሳይ