በጥላቻ የፖለቲካ ትርክቶች ሳይወሰን፣ የልሂቃኑን እና የሕዝቡን አቅም ለአንድ ከፍ ላለ የጋራ ዓላማ ማስተባበር እንደሚገባው ያምናል።ብሔራዊ መግባባት የዘመናት ስብራቶቻችንን ጠግነን ወደ ተሻለ ነገ የምንሻገርበት ብቸኛው ድልድይ መሆኑ አያጠያይቅም።
ፖለቲካዊ መረጋጋት ሳይሰፍን እና በጋራ ጉዳዮቻችን ላይ መግባባት ሳይደረስ አስተማማኝ እና ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን ማረጋገጥ አይቻልም።
ይህን ታላቅ ሀገራዊ አደራ ለመሸከም ደግሞ የመደመር ትውልድ ሚና ወሳኝ እና ታሪካዊ ነው።
የመደመር ትውልድ የትናንት ቁርሾዎችን እና ጥላቻዎችን ተሸክሞ ለመጓዝ የማይፈልግ፣ ይልቁንም በይቅርታ እና በምክክር አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት የተዘጋጀ ንቁ ኃይል ነው።
ይህ ትውልድ ያለፉት ትውልዶች ያጋጠሟቸውን የፖለቲካ ማነቆዎች እና አለመግባባቶች በጥልቀት በመረዳት፣ መፍትሔው የሚገኘው በሀገራዊ ምክክር መድረኮች ላይ መሆኑን በሚገባ ያውቃል።
ልዩነቶችን በኃይል ለመፍታት መሞከር ሀገርን እና ሕዝብን ከማድማት ባለፈ መፍትሔ እንዳላመጣ ከታሪክ ተምሯል።
ስለሆነም በጠረጴዛ ዙሪያ የመቀመጥን፣ የመደማመጥን እና የሐሳብ ልዕልና ባህልን አጥብቆ ይሻል።
ይህ ትውልድ ቁርሾን በይቅርታ ለመተካት ልቡ ክፍት ነው። የቆዩ ታሪካዊ ጠባሳዎችን እና ስብራቶችን በመጠገን፣ የወደፊቱን የጋራ ጉዞ ብሩህ ለማድረግ ይቅርታን እንደ ትልቅ የጥንካሬ እና የብልህነት መገለጫ ይወስዳል።
ሀገራዊ ምክክር የልዩነት ማሳያ ሳይሆን፣ ሕዝባዊ አንድነት እና ኅብረት በጽኑ መሠረት ላይ የሚቆምበት መድረክ እንደሆነም ይረዳል።
በመሆኑም የመደመር ትውልድ በሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ላይ በንቃት በመሳተፍ፣ ጥረቶች እና አቅሞች ሁሉ በአንድ አቅጣጫ እንዲፈስሱ ያደርጋል።
ፖለቲካዊ መረጋጋት እና ሰላም የመንግሥት እና የሕዝብ ሙሉ ትኩረት፣ ሀብት እና ጊዜ ሳይበታተን በልማት እና ብልጽግና ላይ ብቻ እንዲውል ትልቅ ዕድል ይፈጥራል።
ይህን ታሪካዊ ዕድል በሀገራዊ ምክክር ያገኘው እና ሊጠቀምበት የተዘጋጀው ደግሞ የመደመር ትውልድ ነው።
ይህ ትውልድ በትናንት ስህተቶች ከመቆዘም ይልቅ የዛሬን ዕድሎች ተጠቅሞ የነገን ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚተጋ፣ በምክክር የሚያምን፣ በይቅርታ የሚታረቅ እና በጋራ የሚሻገር እውነተኛ የሰላም እና የለውጥ ባለቤት ነው።
በበረከት ሽመልስ