Search

ከቀጣናዊ ተሰሚነት ወደ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪነት፦ የኢትዮጵያ አስደናቂ ጉዞ

ቅዳሜ ሰኔ 06, 2018 47

በኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲ፣ በጸጥታ፣ በአረንጓዴ ልማት፣ በቴክኖሎጂ እና በመሠረተ ልማት ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶች ኢትዮጵያን የአፍሪካ የትኩረት ማዕከል ከማድረግ ባለፈ በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላት ተሰሚነት ከፍ እንዲል አድርገዋል።

በተለይም የሀገር ሉዓላዊነትን እና የቀጣናውን መረጋጋት ለማስጠበቅ የተገነባው ጠንካራ የመከላከያ ሠራዊት ኢትዮጵያን በአፍሪካ ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል ካላቸው ሀገራት መካከል አስቀምጧታል።

መከላከያ ሠራዊቱ ሀገራዊ ደኅንነትን ከማረጋገጥ ባለፈ በተለያዩ የዓለም የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች በመሳተፍ ኢትዮጵያን የዓለም ሰላም አጋር ሀገር ማድረግ ችሏል።

ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አቅምን የተላበሰው የኢትዮጵያ አየር ኃይልም የኢትዮጵያን አየር ክልል 24/7 በተጠንቀቅ በመጠበቅ፣ ፈጣን የአደጋ ምላሽ በመስጠትና የሀገር ሉዓላዊነትን በማስከበር ስትራቴጂያዊ አቋሟን ይበልጥ አጠናክሮታል።

በጸጥታ ዘርፍ የተካሄዱ ሪፎርሞች በፌዴራል ፖሊስ፣ በደኅንነት ተቋማት እና በሌሎችም የሕግ አስከባሪ ተቋማት ተግባራዊ በመሆናቸው ዘመናዊ፣ ተጠያቂነት የተረጋገጠበት እና 24 ሰዓት ለሕዝብ የሚቆም የጸጥታ ሥርዓት ለመገንባት መሠረት ጥለዋል።

ይህም ለኢንቨስትመንት፣ ለቱሪዝም እና ለኢኮኖሚ ዕድገት ምቹ ከባቢ እንዲፈጠር አስተዋጽኦ አድርጓል።

በኢኮኖሚው ዘርፍም ኢትዮጵያ በፈጣን ዕድገት ከሚጠቀሱ የአፍሪካ ሀገራት መካከል ስሟን ማስመዝገብ ችላለች።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች፣ የግብርና ምርታማነት መጨመር፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት፣ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶች እና የግል ዘርፍ ተሳትፎ መጠናከር የሀገራችንን ኢኮኖሚ ወደ አዲስ ምዕራፍ እያሸጋገሩት ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ተፅዕኖ ፈጣሪነት በዲፕሎማሲውም ዘርፍ በግልጽ የሚታይ ነው። አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና ብቻ ሳትሆን ለዓለም አቀፍ ውይይቶች፣ ለንግድ ፎረሞች እና ለሰላም ጉባኤዎች ተመራጭ መዳረሻ ሆናለች።

ይህም የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አቅም ከቀጣናው አልፎ በአሕጉር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጎለበተ መምጣቱን ያሳያል።

በመሠረተ ልማት ዘርፍ ደግሞ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ የኃይል ተስፋ ምልክት ሆኗል። ግድቡ የንፁህ ኃይል ምንጭ በመሆን ለሚሊዮኖች የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ከማሳደግ ባለፈ የአፍሪካ የኢነርጂ ትስስርን የሚያጠናክር ታላቅ ፕሮጀክት ሆኗል።

በአካባቢ ጥበቃ መስክም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ኢትዮጵያን በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ትግል ፊት አውራሪ አድርጓታል።

ሀገራችን በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከልና የአረንጓዴ ልማት ሞዴል በመሆን ቁርጠኝነቷን ለዓለም አሳይታለች። ይህ እንቅስቃሴ የአካባቢ ጥበቃን፣ የምግብ ዋስትናን እና የኢኮኖሚ ጥቅሞችን በአንድ ላይ ያጣመረ ልዩ ተሞክሮ ተደርጎ ይታያል።

በቴክኖሎጂ እና በዲጂታል ሽግግርም ኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ ከፍታለች። የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ስትራቴጂዎች፣ ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎቶች፣ የፈጠራ ማዕከላት እና የቴክኖሎጂ ፓርኮች እየተስፋፉ በመምጣታቸው፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዲጂታል ዘመን ተሳታፊ ብቻ ሳትሆን አቅጣጫ አመላካች ጭምር ለመሆን እየተጋች ትገኛለች።

ዛሬ ኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛቷ፣ በኢኮኖሚዋ፣ በወታደራዊ አቅሟ፣ በዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖዋ እንዲሁም በታዳሽ ኃይል እና በአረንጓዴ ልማት ተሞክሮዋ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ መድረኮች ተፅዕኖ የምታሳድር ሀገር ሆናለች።

በየዘርፉ የተመዘገቡ ስኬቶች የሚያሳዩትም የኢትዮጵያ ጥንካሬ የራሷን ብቻ ሳይሆን የቀጣናውን እና የአፍሪካን የወደፊት ዕድል የሚቀርፅ መሆኑን ነው።

በሀብተሚካኤል ክፍሉ