Search

ዓለም በዝምታ ቢያዘግምም ኢትዮጵያ ምድርን እያከመች ነው!

ቅዳሜ ሰኔ 06, 2018 42

 በዓለማችን ላይ አሳዛኝ እና ዐይን ያወጣ ኢፍትሐዊነት ቢኖር፣ ምድራችንን በበካይ ጋዝ እያፈኗት ያሉት ኃያላን ሀገራት ሲሆኑ፣ የጥፋታቸው ገፈት ቀማሽ ደግሞ ለብክለቱ ኢምንት የማያበረክቱ ደሃ ሀገራት መሆናቸው ነው።

አስቡት፤ አጠቃላይ የዓለማችንን የበካይ ጋዝ ልቀት 75 እስከ 80 በመቶ የሚያመነጩት ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላቸው የቡድን 20 ሀገራት ናቸው።

በአንጻሩ፣ 54 ሀገራትን አቅፋ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት አፍሪካ ለዚህ በካይ ጋዝ ያላት አስተዋፅኦ 3 እስከ 4 በመቶ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያን ጨምሮ አፍሪካውያን ለችግሩ ያበረከቱት አስተዋፅኦ እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም በድርቅ፣ በጎርፍ እና በሙቀት መጨመር ግንባር ቀደም ሰለባ ሆነው ዘመናትን አሳልፈዋል።

የፈረሱ ስምምነቶች እና የወረቀት ላይ ቃላት

የኢንዱስትሪ ባለቤቶች የሆኑት እነዚህ ኃያላን ሀገራት፣ ምድርን በካርቦን ጋዝ እያፈኗት መሆኑን አምነው፣ ልቀትን ለማስቀረትና ለችግሩ ሰለባ ለሆኑት ሀገራት ካሳ ለመክፈል በፓሪስ ታሪካዊ ስምምነት ፈረሙ።

ነገር ግን ዘመናት ተቆጠሩ፤ የወረቀት ላይ ቃላት ወደ ተግባር ሳይቀየሩ፣ ስምምነቶች የሚዲያ ፍጆታ ብቻ ሆነው ቀሩ። በኃያላኑ ቸልተኝነትና ቃል ማጠፍ ምክንያት ዓለማችን በድርቅ፣ በጎርፍ መጥለቅለቅ፣ በበረሃማነት መስፋፋት እና ባልተጠበቀ የአየር ጸባይ መዛባት ክፉኛ መታመሷን ቀጥላለች።

ከንግግር ወደ ተግባር፤ የኢትዮጵያ አረንጓዴ አብዮት

ዓለም መፍትሔ አጥቶ በየስብሰባ አዳራሹ ሲባዝን፣ ቃሉን ሲያጥፍና ከንግግር ያለፈ አንዳች መፍትሔ ማምጣት ሲሳነው፣ ኢትዮጵያ ግን እጆቿን አጣጥፋ የኃያላኑን ምፅዋት አልጠበቀችም። ይልቁንም ተፈጥሮን እና አካባቢን ለማከም ቆርጣ በመነሳት ዓለምን ያስደመመ ተዓምራዊ የድል ትርክት መፃፍ ጀመረች።

ይህ ታሪካዊ የአረንጓዴ ዐሻራ ጉዞ፣ 2011 . በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (/) አነሳሽነት በይፋ ሲበሰር፣ ገና በዕለቱ 350 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀንበር በመትከል የህንድን የዓለም ክብረ-ወሰን በታላቅ ጀግንነት በመስበር ነበር የተጀመረው።

ዓለም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክፉኛ በተረበሸችበት 2012 . እንኳን፣ ኢትዮጵያውያን ተስፋ ሳይቆርጡ 5 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ጽናታቸውን አሳይተዋል። 2013 እና 2014 . 6 ነጥብ 8 እና 7 ነጥብ 2 ቢሊዮን በላይ ችግኞች በምድሪቱ ላይ ሲያርፉ፣ እንደ ሐሮማያ ሐይቅ ያሉ ጠፍተው የነበሩ የውሃ አካላት ዳግም ህያው ሆነዋል።

የድል መዳረሻዎቻችን በዚህ አላበቁም፤ 2015 . ለምግብ ዋስትና የሚሆኑ የፍራፍሬ ተክሎች ላይ በማተኮር 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች ተተከሉ። 2016 . ይህ አሃዝ ወደ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሲሻገር፣ በአንድ ጀንበር ብቻ 600 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል የራሳችንን ክብረ-ወሰን ደግመን ሰበርን።

በመጨረሻም 2017 . 8 ቢሊዮን በላይ ዐሻራዎችን በማኖር፣ በሰባት ዓመታት ጉዞ ብቻ 48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ኢትዮጵያ በዓለም የደን ልማት መዝገብ ላይ ወደር የማይገኝለት የልዕልና ስፍራ ተቀመጠች። በየዓመቱ 25 እስከ 35 ሚሊዮን ዜጎች በፈቃደኝነት የሚሳተፉበት ይህ ግዙፍ ንቅናቄ፣ ብሔራዊ አንድነትን ያጠናከረ የአረንጓዴ ማዕበል ሆኗል።

ይህ 7 ዓመታት ጉዞ ያመጣው ሥነ-ምህዳራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተዓምር ቃላት ከሚገልጹት በላይ ነው። አስቀድሞ ወደ 3 በመቶ አሽቆልቁሎ የነበረው የሀገራችን የደን ሽፋን፣ በማይታመን ፍጥነት አድጎ 23 ነጥብ 6 በመቶ ደርሷል።

የተተከሉት ችግኞች 80 እስከ 85 በመቶ በሚደርስ የፅድቀት ምጣኔ ጸድቀው፣ በአማካይ 64 ሚሊዮን በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች የሚያወጡትን በካይ ጋዝ ከከባቢ አየር ላይ በማጽዳት ዓለምን እየታደጉ ይገኛሉ።

መሬቱ ውሃን የመምጠጥ አቅሙ 16 ነጥብ 9 በመቶ ወደ 68 ነጥብ 9 በመቶ በከፍተኛ ደረጃ በማደጉ፣ የተፋሰስ ልማቱ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የሌሎች የኃይል ማመንጫ ግድቦችን የዕድሜ ጣሪያ ቢያንስ 50 ዓመታት እንዲራዘም አድርጓል።

ከዚህም ባሻገር በተቋቋሙ 120 ሺህ በላይ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ለሚበልጡ ዜጎች የስራ ዕድል ሲፈጠር፤ ተፈጥሮ በማገገሟም የሀገራችን የቡና ወጪ ንግድ 230 ሺህ ቶን ወደ 475 ሺህ ቶን በማደግ ትልቅ የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ ነው።

በአጠቃላይ፣ ኃያላን ሀገራት ዛሬም ስለ አየር ንብረት ለውጥ ይነጋገራሉ፣ ስምምነት ያፈርሳሉ፣ ይከራከራሉ። ኢትዮጵያ ግን ንግግርን ወደ ተግባር ቀይራ፣ ቆስላ የነበረችውን ምድር በቢሊዮኖች አረንጓዴ ዐሻራ በተግባር እያከመች ነው።

አረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ የመትከል ዘመቻ ብቻ ሳይሆን፣ ተፈጥሮን ማዳን፣ ማክሮ-ኢኮኖሚን መገንባት እና ትውልድን ማሻገር መሆኑን አሃዞች አፍ አውጥተው እየመሰከሩ ነው።

የዓለምን የሥነ-ምህዳር ህመም ለመፈወስ እውነተኛው እና ህያው መድኃኒት ከኢትዮጵያ ተገኝቷል፤ ወደ 50 ቢሊዮን የሚያልመው የድል ትርክታችንም በብልጽግና ጎዳና ላይ አሁንም ተጠናክሮ ይቀጥላል።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ