ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ16 የተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ተመራማሪዎችና የፈጠራ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት ዓለም አቀፍ የምርምር ጉባዔና የቴክኖሎጂ ውድድር፣ ዛሬ በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ተጀምሯል።
የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ያዘጋጀው ይህ መድረክ፤ "መጻኢ የክህሎት ልማትና ቴክኖሎጂያዊ ፈጠራን ያቀፈ ዘላቂ የኢንዱስትሪ ሽግግር" በሚል መሪ ቃል ለተከታታይ 3 ቀናት የሚቆይ ይሆናል።
በጉባዔው ላይ ከጀርመን፣ ሕንድ፣ ቻይና፣ ኢራን እና ናይጄሪያ ጨምሮ ከ16 የዓለም አገራት የመጡ እንግዶችና ተሳታፊዎች ተገኝተዋል። በመድረኩም 30 የምርምር ፅሁፎች የሚቀርቡ ሲሆን፣ ከ35 በላይ አዳዲስ የፈጠራና የቴክኖሎጂ ስራዎች ለውድድር ቀርበዋል።
በአካልና በበይነ-መረብ እየተካሄደ በሚገኘው በዚህ መድረክ ላይ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት በተጨማሪ፣ የኢንዱስትሪ አመራሮች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወካዮች፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ተመራማሪዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት በምርምርና ቴክኖሎጂ ልማት ላይ ትኩረት በማድረግ ዘመኑን የዋጁ ስልጠናዎችን ከመስጠት ባለፈ፣ የፖሊሲ ጥናቶችን በማካሄድ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥነ-ምህዳር እንዲጎለብትና የተኪ ምርቶች ምርታማነት እንዲያድግ እየሰራ መሆኑ ተመላክቷል።
በዓድዋ ድል መታሰቢያ የተከፈተው ይህ ዓለም አቀፍ መድረክም፣ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን አቅም ለማጠናከርና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ለመቀመር ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡
በበይነ-መረብ በተሰጠ ስልጠና ላይ የማሰልጠኛ ተቋማት የኢንዱስትሪ 4.0፣ 5.0 እና 6.0 ሽግግሮችን መደገፍ የሚችሉ በቴክኖሎጂና በፈጠራ የበለጸጉ ባለሙያዎችን በማፍራት ላይ ማተኮር እንደሚገባቸው ተጠቁሟል፡፡
ጉባዔው በኢትዮጵያ የተጀመሩ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሥራዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ልምድ የሚቀሰምበት እንዲሁም በተመራማሪዎች፣ በፖሊሲ አውጪዎችና በልማት አጋሮች መካከል ጠንካራ ትስስር የሚፈጠርበት መድረክ እንደሚሆን ይጠበቃል።