ዓለምን እጅግ ሊያሳስባት እና የሰው ልጅ አጥብቆ ሊጠነቀቅለት የሚገባው የአየር ንብረት ለውጥ፣ በአሁኑ ሰዓት ከሙቀት መጨመር እና ከአካባቢ መዛባት ተሻግሮ የምድርን የ24 ሰዓት የቀን ርዝማኔ እየለወጠው መሆኑን አዳዲስ ሳይንሳዊ ጥናቶች አረጋግጠዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ የምድርን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ የፕላኔቷን እሽክርክሪት እያዘገመው መሆኑን ፎርብስ መጽሔት በስፋት አስነብቧል።
የቪየና ዩኒቨርሲቲ እና የኢቲኤች ዙሪክ (ETH Zurich) ተመራማሪዎች ይፋ ባደረጉት የጋራ ጥናት መሠረት፣ በዋልታዎች አካባቢ የሚገኙ ግግር በረዶዎች በከፍተኛ ፍጥነት መቅለጥ ለዚህ ታሪካዊ ክስተት መነሻ ሆኗል።
በረዶው ቀልጦ ወደ ውቅያኖስ ሲቀላቀል ከፍተኛ መጠን ያለው ውኃ ከዋልታዎች ወደ ምድር ወገብ ይሰበሰባል።
ይህ የክብደት ስርጭት መዛባት የምድርን የመዞር ፍጥነት እንዲቀንስ እና ቀናት ከወትሮው እንዲረዝሙ ምክንያት ሆኗል።
የቀን ርዝማኔ ለውጡ ምንም እንኳ በሚሊሰከንዶች (ከአንድ ሰከንድ ሺህ እጅ) የሚቆጠር ቢሆንም፣ በዘመናዊው ዓለም ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እጅግ የጎላ ነው።
በተለይም እጅግ ጥቃቅን የጊዜ ሰሌዳ ላይ ተመሥርተው በሚሠሩ የጂፒኤስ (GPS) የሳተላይት አሰሳዎች፣ የሕዋ ተልዕኮዎች፣ የፋይናንስ ዝውውሮች እና በዓለም አቀፍ የኮሙኒኬሽን ሥርዓቶች ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል ሊፈጥር እንደሚችል ተመራማሪዎቹ አስጠንቅቀዋል።
የበካይ ጋዝ ልቀት አሁን ባለው አስደንጋጭ ፍጥነት የሚቀጥል ከሆነ፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ጨረቃ በምድር ላይ ካላት የተፈጥሮ ስበት በበለጠ ቀናትን የማራዘም አቅም እንደሚኖረው ጥናቱ አረጋግጧል።
የአየር ንብረት ለውጥ በምድር የመዞር እና የጊዜ ርዝማኔ ላይ ሳይቀር እያሳደረ ያለው ተፅዕኖ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ በከተተበት በአሁኑ ወቅት፣ ኢትዮጵያ እያከናወነቻቸው የሚገኙት አረንጓዴ የልማት ሥራዎች ተስፋ ሰጪ እና አበረታች ናቸው።
ሀገራችን ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚከሰቱ ጫናዎችን ለመከላከል 48 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን በስኬት እየተገበረች ትገኛለች።
ከዚህም ባለፈ ከነዳጅ ተሽከርካሪዎች የሚወጣውን በካይ ጋዝ ለማስቀረት፣ በአረንጓዴ ትራንስፖርት ወደ አረንጓዴ ኢኮኖሚ በፍጥነት በመሸጋገር ላይ ትገኛለች።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታዋን ከውኃ፣ ንፋስ እና ጂኦተርማል በመሳሰሉ ታዳሽ የኃይል ምንጮች የምታመነጭ በመሆኗ፣ የካርቦን ልቀትን በመቀነስ ረገድ ለዓለም አርአያ የሚሆን ተግባር እያከናወነች ነው።
የጊዜን ስሌት እስከመቀየር የደረሰን የተፈጥሮ መዛባት መቋቋም የሚቻለው በወረቀት ላይ በሚቀሩ ስምምነቶች ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ ተግባራዊ እያደረገች እንዳለው ዓይነት መሬት ላይ በሚታዩ ተጨባጭ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ብቻ ነው።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ