Search

በቻይና መኪና እና ሰማይን የሚያገናኝ የቴክኖሎጂ የሙከራ ማዕከል ሥራ ጀመረ

ሓሙስ ግንቦት 27, 2018 96

በደቡብ ቻይና ጓንግዶንግ ግዛት ውስጥ መኪናዎችን በምድር ላይ ብቻ ሳይሆን በሰማይም ላይ ጭምር ለመፈተሽ የሚያስችል ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ማዕከል ሥራ ጀምሯል፡፡

"የደቡባዊ ስማርት የተሳሰሩ አዳዲስ የኃይል ማመንጫ ተሽከርካሪዎች የሙከራ ማዕከል" የተሰኘው ይህ ተቋም፣ በሀገሪቱ የመጀመሪያው ብሔራዊ ደረጃ "የመንገድ እና የአየር የተቀናጀ" የሙከራ ቦታ ነው፡፡

ይህ ማዕከል መኪና እና ሰማይ የሚገናኙበት ከመሆኑም በላይ በትራንስፖርትና በቴክኖሎጂ የሙከራ ሂደት ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ተቋም ሆኗል፡፡

ማዕከሉ 8,600 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፣ ወደ 100 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የጸደቀ የአየር ክልልም አለው ተብሏል፡፡ 

ይህ ግዙፍና ዘመናዊ ተቋም ማንኛውንም ዓይነት የተሽከርካሪ ሙከራዎችን በተሟላ ሁኔታ ለማከናወን ታስቦ የተገነባ ነው፡፡

በተለይም ማዕከሉ ለሦስት ዋና ዋና የሙከራ ዓይነቶች አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ እነሱም የተለመዱ የመኪናዎችን ብቃት ማረጋገጥ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እርስ በርስ የተሳሰሩ ስማርት መኪናዎችን መፈተሽ እና ወደፊት አገልግሎት ላይ ለሚውሉ "የሚበሩ መኪኖች" የዝቅተኛ ከፍታ በረራ ሙከራዎችን በሰማይ ላይ ማድረግ ናቸው፡፡

ዚህ ታላቅ የቴክኖሎጂ ፍተሻ ይረዳ ዘንድ ተቋሙ እጅግ አስደናቂ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን በውስጡ አካትቷል፡፡

ከእነዚህም መካከል 8,500 ሜትር ርዝመት ያለው የከፍተኛ ፍጥነት የክበብ መንገድ፣ 300 ሜትር ዲያሜትር ያለው ተንቀሳቃሽ መናፈሻ ወይም ፕላዛ፣ 1,800 ሜትር ርዝመት ያለው የመኪና ብቃት ማሳያ መንገድ እና መኪኖቹ በተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንዲፈተሹ ለማድረግ 34 የተለያዩ ልዩ ልዩ የገጽታ ዓይነቶችን ያካተተ ሰፊ የመንገድ አውታር በዋናነት ይገኙበታል፡፡