የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) የምርጫ ታዛቢ ቡድን አዲስ አበባ ለሁለት ቀናት የቆየውን ከፍተኛ የዝግጅት እና የገለጻ ፕሮግራም ካጠናቀቀ በኋላ፣ የምርጫ ታዛቢ ቡድኑን ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች ማሰማራቱን ገልጿል።
የምርጫ ታዛቢ ቡድኑ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ያደረገው ገለጻ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ወሳኝ ምዕራፍ ነው ተብሏል።
ለታዛቢ ቡድኑ የተደረገው የገለጻ ፕሮግራም፣ ታዛቢዎቹ በምርጫው ዕለት ሊጠቀሙባቸው የሚገቡ የክትትል ሰነዶች፣ የፀጥታ ሥነ-ሥርዓቶች እና የሎጂስቲክስ ዝግጅቶችን በተቀናጀ እና ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲመሩ የሚያስችል ግንዛቤ የፈጠረ መሆኑ ነው የተገለጸው።
የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ስፔሲዮዛ ዋንዲራ-ካዚብዌ (ዶ/ር) ስምሪቱን በሰጡበት ወቅት ባስተላለፉት መመሪያ ታዛቢዎቹ ከፍተኛ የሥነ-ምግባር ደረጃን እንዲጠብቁ አሳስበዋል።

የምርጫ ታዛቢ ቡድኑ ስኬት በሙያዊ ብቃት፣ ፍጹም ገለልተኝነት እና ዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢነት መርሆዎችን በጽኑ መከተል ላይ የተመሠረተ እንዲሆን አሰሳበዋል።
ከሁለት ቀናት ዝግጅተ በኋላ የታዛቢ ቡድኖቹ ወደ ተመደቡባቸው የክልል ጣቢያዎች ጉዟቸውን ጀምረዋል።
ታዛቢዎቹ ኢትዮጵያ ወደ ምርጫ በምትጓዝበት በዚህ ወቅት የምርጫው ሂደት ግልጽነት እና ፍትሐዊነት የተላበሰ እንዲሆን የመጨረሻዎቹን ዝግጅቶች እንደሚከታተሉ ይጠበቃል።
በላሉ ኢታላ