የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀደም ሲል ባስታወቀው መሰረት ወደ ደብረ ማርቆስ ከተማ የሚያደርገውን የቅድመ ምረቃ በረራ ዛሬ በይፋ መተግበር ጀምሯል።
በረራው በአካባቢው ነዋሪዎች፣ ተጓዦች እና የአየር መንገዱ ሠራተኞች ዘንድ ከፍተኛ ደስታ ፈጥሯል።
በመጀመሪያው በረራ የተሳፈሩ ተጓዦች አዲሱ አገልግሎት ለከተማው እና ለአካባቢው ሕዝብ ትልቅ እፎይታ እንደሚያመጣ ገልጸዋል።
“ከዚህ በፊት ለአየር ጉዞ ወደ ባሕር ዳር መጓዝ ይኖርብን ነበር። አሁን ግን ከደብረ ማርቆስ በቀጥታ መጓዝ መቻላችን ጊዜን እና ወጪን ይቆጥባል” ሲሉ ተጓዥ ተናግረዋል።
በበረራው ላይ የተሳተፉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች በበኩላቸው ደብረ ማርቆስን በአየር መንገዱ የበረራ መዳረሻዎች ዝርዝር ውስጥ ማካተት የተቋሙ የአገልግሎት ማስፋፊያ አካል መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ በረራ ለአካባቢው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለንግድ እና ለልማት እንቅስቃሴዎችም አዲስ እድል ይፈጥራል።
በቅድመ ምረቃ በረራው የተገኘው ስኬት ደብረ ማርቆስ ወደ ሀገራችን የአየር ትራንስፖርት አውታረ መረብ በይፋ የምትቀላቀልበትን አዲስ ምዕራፍ እንደሚያመላክት ከአማራ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።