የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚደረገው ውይይት መሻሻል እንዳሳየ እና ከስምምነት ሊደረስ እንደሚችል በመግለፅ በኢራን ላይ ሊሰነዝሩት ያሰቡትን ጥቃት ማቋረጣቸውን አስታውቀዋል።
ትራምፕ ትናንት ሐሙስ ኻርግ ደሴት ላይ ኢራንን “ክፉኛ እንመታለን” ብለው ቢዝቱም፤ ሊያደርሱት የነበረውን ጥቃት ለመሰረዝ መወሰናቸውን ነው የተናገሩት።
ከኢራን ጋር የሚፈረመው የመግባቢያ ሰነድ “የመጨረሻ ደረጃ” ላይ መድረሱን ጠቅሰው በዚህ ሳምንት ስምምነቱ ሊገባደድ እንደሚችል አስረድተዋል። ስምምነቱ የሚፈረመው አውሮፓ ውስጥ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
ስምምነቱ ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ እንዳይኖራት የሚያግድ እንዲሁም በአፋጣኝ የሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲከፈት የሚያስገድድ እንደሚሆን ትራምፕ አስረግጠው ተናግረዋል።

ትራምፕ ይህንን ቢሉም የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ስምምነት ላይ ለመድረስ አለመቃረባቸውን አስታውቀዋል።
አሜሪካ በድርድሩ “ከልክ ያለፈ ጥያቄ” እያቀረበች እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ኳታር ሁለቱን አገራት ለማሸማገል ጥረት እያደረገች እንደሆነ ተጠቁሟል።
ትራምፕ ኢራን ላይ ጥቃት እንደማይፈጸም መግለጻቸውን ተከትሎ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ቅናሽ ማሳየቱን የዘገበው ቢቢሲ ነው ።