የዓድዋ ድል የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ኩራት የሆነው በጀግኖች አባቶቻችን እና እናቶቻችን የተባበረ ክንድ ነው። የአመራር ብቃታቸው እና ኅብረታቸው ደግሞ ለአንጸባራቂው ድል የላቀውን ድርሻ ተወጥቷል። ዛሬ ለድሉ የማይረሳ አሻራ ጥለው ያለፉትን አሥራ ሁለቱን የጦር መሪዎች ታሪክ በአጭሩ እናስታውሳለን።
ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል (አባ ቃኘው)፦ ዲፕሎማቱ ጄኔራል
የሐረር ገዥ እና የአፄ ምኒልክ የአጎት ልጅ የነበሩት ልዑል ራስ መኮንን ስልታዊ የጦር መሪ ነበሩ። ከዋናው ጦርነት በፊት በአምባላጄ ጦርነት ጣሊያንን በድንገተኛ ጥቃት በመምታት ትልቅ ድል አስመዝግበዋል።
በዓድዋ ጦርነት ወቅት 15 ሺህ የሚጠጋ ዘመናዊ ጦር በመምራት የጣሊያንን ብርጌዶች በመከፋፈል አዳክመዋል። የጄኔራል አልበርቶኒን ጦር በመደምሰስ ለድሉ መፋጠን ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።
ራስ አሉላ እንግዳ ቁቢ (አባ ነጋ)
ከዓድዋ በፊት በዶጋሊ ጦርነት ጣሊያንን ያስጨነቁ አንበሳ ነበሩ። በጦርነቱ ወቅት በዘረጉት የስለላ መረብ ጣሊያኖች የካቲት 22 ቀን ሌሊት መነሳታቸውን ለኢትዮጵያ ጦር ቀድመው በማሳወቅ ዝግጁነትን ፈጥረዋል። በግንባሩም ወራሪውን እረፍት በማሳጣት ለአንጻባራቂ ድል የላቀ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ከዓድዋ በፊት ከግብፆች እና ማሃዲስቶች ጋር ሦስት ታላላቅ ጦርነቶችን አድርገው በድል የተወጡ የኢትዮጵያ ጠላቶችም የሚያነድ ክንዳቸውን የቀመሱ ጀግና ናቸው።
ራስ መንገሻ ዮሐንስ (አባ ግጠም)
የአፄ ዮሐንስ 4ኛ ልጅ ሲሆኑ፣ የግል ቅሬታቸውን ትተው ለሀገር አንድነት ከአፄ ምኒልክ ጋር በጽናት ተሰልፈዋል። በዓድዋ ጦርነት 12 ሺህ ጦራቸውን መርተው በብርቱ ተዋግዋል። የኢትዮጵያ ጦር ወደ ቦታው ከመድረሱ በፊትም የጣሊያን ጦር የበለጠ እንዳይገፋ ይዘውት የቆዩት እኒሁ የሀገር ነጻነትን ከግል ሥልጣን ያስበለጡት የኢትዮጵያ ባለውለታ ናቸው።
ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ተሰማ (አባ ጠና)
የጎጃሙ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ለሀገር ክብር ሲሉ 20 ሺህ የሚጠጋ ጦር ይዘው ወደ ዓድዋ ዘምተዋል። በጦርነቱ መጀመሪያ አካባቢ ከጣሊያን የፊት ጦር ጋር በፅናት በመጋፈጥ የጠላትን ወኔ ሰብረዋል። ፈረሰኞችን ከእግረኞች አዋህደው በመምራት ለድሉ ወሳኝ ሚና የተጫወቱ ሌላው የሀገር ባለውለታ ናቸው። ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትም ለሀገር ነጻነት ሲሉ የሥልጣን ሽኩቻውን ወደ ጎን ትተው ለኢትዮጵያ ደጀን የሆኑ ትውልድ የማይረሳቸው የኢትዮጵያ ጀግና ናቸው።
ራስ ሚካኤል አሊ ሊበን (አባ ሻንቆ)
የወሎው መሪ ራስ ሚካኤል 6 በላይ ስመ ጥር ፈረሰኞችን ይዘው ተሳትፈዋል። የጦርነቱ ማብቂያ አካባቢ "እባልጉሜ! እባልጉሜ!" (እጨደው!) በሚል የጦር ጩኸት በማጥቃት የጄኔራል ዳቦርሚዳን ጦር ሙሉ በሙሉ ደምስሰዋል ። ይህ ጥቃት የጣሊያንን ጦር መፈራረስ አረጋግጧል።
ፊታውራሪ ገበየሁ ገቦ ጉርሙ (አባ ጎራ)
የጠላትን አደገኛ አድብቶ የማጥቃት እቅድ በመረዳት፣ ራሳቸውን መስዋዕት አድርገው የፊት መስመሩን በመክፈት ጦሩ ሳይደናቀፍ እንዲሰለፍ አድርገዋል። በተለይም በአምባላጄው ጦርነት ቀድሞ ቦታ የያዘው ጣሊያን በወገን ላይ ባደረሰው ጥቃት ጦሩ መፈታት ሲጀምር ራሳቸው ፊት ለፊት ገጥመው የጠላትን ኃይል አፍረክርከዋል። በዚሁ ጦርነት በጀግንነት ተሰውተዋል።
ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ (አባ ነፍሶ)
በመድፍ ተኳሽነት የተሰለፉት ባልቻ፣ መድፈኞቹ ሲወድቁ ራሳቸው መድፉን በመተኮስ የጣሊያንን ምሽግ ያፈራረሱ ድንቅ ጀግና ናቸው። በተለይም ፊታውራሪ ገበየሁ በአምባላጄው ጦርነት ሲሰው ደጃዝማች ባልቻ ኃላፊነቱን በመቀበል የጠላትን ጦር እንደ ሰደድ እሳት ለብልበዋል።
ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ (አባ መላ)
አባ መላ በዓድዋ ጦርነት የቤተ መንግሥቱን ጦር በመምራት ነው የተሳተፉት። የአፄ ምንልክ አብሮ አደግ እና ቀኝ የተባሉት ፊታውራሪ ገበየሁ ሲሰውም እርሳቸውን በመተካት የንጉሡን ጦር አስተባብረዋል። ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ከጦር መሪነታቸው ባሻገርም በብልሃት አዋቂነታቸው አባ መላ የሚለው ስም ተሰጥቷቸዋል። በወጣትነታቸው በጀግንነት እና በብልሃት የተሳተፉት ፊታውራሪ፣ በኋላም የኢትዮጵያ መከላከያ እንዲዘምን ትልቅ አሻራ ጥለዋል።
ራስ አባተ ቧያለው (አባ ይትረፍ)
ታዋቂ የመድፍ አዛዥ እና የቅርብ ከአፄ ምኒልክ የጦር መሪዎች አንዱ ነበሩ። በዓድዋ ጦርነት ወቅት የመድፍ ጦሩን በብቃት በመምራት የጠላትን ምሽግ በማፈራረስ እና ጦሩ ወደፊት እንዲገሰግስ በማድረግ ከፍተኛ ጀግንነት ፈጽመዋል። የጦሩ ገበሬ አባ ይትረፍ በመድፍ ተኳሽነታቸው የጠላትን ጦር ሰፈር በማቃጠል ድሉ ለወገን እንዲሆን የላቀ ድርሻቸውን ተወጥተዋል።
ራስ ወሌ ብጡል ኃ/ማርያም (አባ ጠጣው)
የየጁ ገዥና የእቴጌ ጣይቱ ወንድም የነበሩት ራስ ወሌ፣ ከየጁና ከወሎ የተውጣጣውን እጅግ ግዙፍ ጦር በመምራት ዘምተዋል ። በአምባላጌና በመቀሌ ጦርነቶች ላይ የጠላትን ኃይል በመዳከም ረገድ ጉልህ ሚና የነበራቸው ሲሆን፣ በዓድዋም ግንባር ቀደም ተሰላፊ ነበሩ።
ራስ ብትወደድ መንገሻ አቲከም (አባ ገድብ)
የአገው ምድር እና የዳሞት ገዥ የነበሩት ራስ መንገሻ፣ ለአፄ ምኒልክ እጅግ ታማኝ እና ብርቱ የጦር መሪ ነበሩ። በዓድዋ ጦርነት ወቅት ከ6 ሺህ በላይ የሚሆን ጦር በማሰለፍ በስተቀኝ በኩል ያለውን ግንባር በፅናት በመከላከል እና በማጥቃት ድል አስመዝግበዋል። ጄኔራል ቶዜሊ የተባለው የጣሊያን ጦር መሪ በተገደለበት ግንባር የወገን ጦር አንጸባራቂ ድል እንዲያገኝ ወሳኝ ድርሻ የነበራቸው እኒሁ ጉምቱ መሪ ናቸው።
ዋግሹም ጓንጉል ብሩ (አባ መርከብ)
የዋግ ግዛት መሪ የነበሩት ዋግሹም ጓንጉል፣ ከ10 እስከ 11 ሺህ የሚሆነውን የዋግን ጦር በማሰለፍ በዓድዋ ምድር በጀግንነት ተዋግተዋል። የጠላትን ጦር ከመሃል እና ከጎን በመቁረጥ ረገድ የጦራቸው ተሳትፎ ለድሉ መጠናቀቅ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው። በአምባላጄ ጦርነትም ከራስ መንገሻ ዮሐንስ ጦር ጎን በመሰለፍ ዓይን ከፋች ለሆነው የአምባላጄ ድል አስተዋጽኦ አድርገዋል። በማርያ ሸዊቶ በኩል የተሰለፈውን እና በጄኔራል አልቤርቶኒ ጦር በመበተን ጄኔራሉም እንዲማረክ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ ከ4 መቶ በላይ የጣሊያን ወታደሮች እና ባለ ማዕረግ መሪዎችን ማርከዋል።
በለሚ ታደሰ