በአዋሽ አርባ ጊዜያዊ የዲሞብላይዜሽን ማዕከል በሱዳን ለነበሩና ወደ ሀገር ቤት ለተመለሱ፣ በተለምዶ አጠራሩ "አርሚ 70" ተብሎ ለሚታወቀው የቀድሞ ታጣቂዎች ሲሰጥ የቆየው የተሀድሶ ሥልጠና በዛሬው ዕለት ተጠናቋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብረሀም በላይ (ዶ/ር)፤ የትግራይ ሕዝብ አሁን ላይ የሚሻው ሰላም መሆኑን ገልጸው፣ ወጣቱ ከሞት ተርፎ ወደ ሰላም መምጣቱ ትልቅ ድል መሆኑን ተናግረዋል።
መንግሥት በትግራይ ሰላምና ልማት እንዲሰፍን በትኩረት እየሠራ ቢሆንም፣ የሕወሓት ቡድን እንቅፋት እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል። በመሆኑም ሕዝቡ በሐሰት ወሬ ሳይደናገር ከመንግሥት ጎን ሆኖ ልማቱን እንዲያፋጥን ጥሪ አቅርበዋል።
የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጄነራል ደርቤ መኩሪያ በበኩላቸው፤ ሥልጠናውን ያጠናቀቁት ከ500 በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
የሥልጠናው ተሳታፊዎች መንግሥት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት አድንቀው፤ በተወሰኑ ግለሰቦች ምክንያት ሰቆቃ ውስጥ ለሚገኘው የትግራይ ሕዝብ ዘላቂ መፍትሔ እንዲበጅለት ጠይቀዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎቹ ባለ 11 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት፤ ጦርነትን የሚጸየፍ ትውልድ ለመገንባትና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በወንድወሰን አፈወርቅ